በተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ

138

ደብረ ማርቆስ፣ ታህሳስ 2/2013 (ኢዜአ )  በምስራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ትላንት ሌሊት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። 

በሁለት የቤተሰብ አባላት ላይም ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኅላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው ደብረ ያዕቆብ ቀበሌ ትላንት ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ አደጋው ደርሷል።

በአደጋው ህይወታቸውን ያጡና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከደቡብ ወሎ ዞን መከነ ሰላም ከተማ ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-78171 አዲስ አበባ የሆነ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ከመንገድ ወጥቶ በመገልበጡ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ የስድስት ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ገልጸዋል።

በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመርጦ ለማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የሟቾች አስከሬን ለየቤተሰባቸው ለመላክ ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

"የቤተሰብ አባላቱ በመካነ ሰላም ከተማ ለቅሶ ደርሰው በጎጃም በኩል ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ እንዳሉ ለአደጋው ተጋልጠዋል " ብለዋል።

አደጋው በሌሊት በሚደረግ ጉዞ የተፈጠረ በመሆኑ የከፋ አድርጎታል ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ ማህበረሰቡ ከመሰል የሌሊት ጉዞ በመጠንቀቅ አደጋን መከላከል እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም