በነቀምት ከተማ ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ነዋሪዎች የስራ እድል ተፈጥሯል

59
ነቀምቴ ሀምሌ 12/2010 በነቀምት ከተማ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ነዋሪዎች የስራ እድል መፈጠሩን የከተማዋ  የስራ እድል ፈጠራ እና የከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የማህበራት ህጋዊነት የስራ ሂደት መሪ አቶ ገረመው ሂርጳ እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ 8 ሺህ 500 ዜጎችን በተለያየ የስራ ዘርፍ ለማሰማራት ታቅዶ ለ7 ሺህ 300 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 872 የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ናቸው። የስራ እድሉ የተፈጠረላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች መካከል አገልግሎት፣ የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ፣ ኮንስትራክሽን፣ አነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ይገኙበታል። የስራ እድሉ ተጠቃሚዎች በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ በተደረገው ጥረት ለ270 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ፣ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች ተገንብተው መሰጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ገረመው ገለፃ ከወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የተገኘውን 22 ሚሊዮን ብር ጨምሮ 45 ሚሊዮን ብር ብድር የተሰራጨ ሲሆን ለምርቶቻቸውም 113 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተመቻችቷል፡፡ በነቀምት ከተማ ከስራ እደሉ ተጠቃሚዎች መካከል የቡርቃ ጃቶ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ብርሃኑ ቡሊ በሰጡት አስተያየት በቴክኒክና ሙያ ቢመረቅም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራ አጥ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ አመት ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በማህበር ተደራጅተው መንግስት ባመቻቸላቸው 100 ሺህ ብድር ምግብ ቤት ከፍተው እየሰሩ መሆኑን ገልጿል። ወጣት ዮሐንስ ድሳሳ በበኩሉ በ2006 ዓ.ም በ40 ሺህ ብድር ሁለት ሆነው የጀመሩት የእንጀራ ምጣድና ስቶፍ ምርት ስራ ዛሬ ላይ ካፒታላቸውን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ አስችሏቸዋል። ብድራቸውን በመመለስ ባፈሩት ሀብትም በነፍስ ወከፍ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት በመገንባት በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል። ቀደም ሲል የቤተሰብ እጅ ይጠብቅ እንደነበር የሚናገረው ወጣቱ በፈጠሩት ስራም ለሁለት ግለሰቦች የስራ እድል ፈጥረዋል። በነቀምት ከተማ ዘንድሮ 67 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 64 ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም