ለስራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለሚሄዱ ዜጎች መረጃ የሚሰጥ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

120

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2013(ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለሥራ ለሚሄዱ ዜጎች መረጃ የሚሰጥ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ። 

''የጉዞ ስንቅ'' ተብሎ የተሰየመውን የሞባይል መተግበሪያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም የሠራተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር አዘጋጅቶታል።       

አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን የሚጠቀመው መተግበሪያው ዜጎች ለሥራ ወደ ውጭ አገራት ከመሄዳቸው በፊት፣ በሥራ ላይ ሆነውና ከሥራ በኋላ ስለሚከውኗቸው ተግባራት መረጃ ይሰጣል።        

በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ መንገዶች ወደ ባህሬን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና ሌሎችም አገራት ለሥራ ይጓዛሉ።   

ነገር ግን ስለሚሄዱበት አካባቢ፣ ስለሚያከናውኑት ሥራ፣ ስለሚኖራቸው ኃላፊነትና መብት አስፈላጊ መረጃ ባለመያዛቸው ለችግር ይዳረጋሉ።          

ወደ አገራቱ የሚሄዱት ተጓዦች የጉዞ ስንቅ መተግበሪያን ወደ ስልካቸው አውርደው በመጠቀም ግንዛቤያቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ተገልጿል።    

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደተናገሩት "ዜጎች ወደ ሥራ መዳረሻ አገራት ከመጓዛቸው በፊት በቂ መረጃ ሊኖራቸው ይገባል"።

መረጃ አቅምና ዕውቀት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ዜጎች ወደ አገራቱ ከመሄዳቸው በፊትና በኋላም የሚያስፈልጓቸውን መረጃዎች ለማግኘት የመተግበሪያው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።  

ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለፈው ዓመት በመንግሥት አመቻቺነት 16 ሺህ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ዓረብ አገራት መሄዳቸውን አስታውሰዋል።     

ዜጎች የሚደርሱባቸውን ችግሮች የሚያስቀሩት በሕጋዊ መንገድ ብቻ በመጓዝ መሆኑን እንዲያውቁ  ከክልሎች ጋር በመተባበር ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል።  

በኢትዮጵያ የዓለም የሠራተኞች ድርጅት ተወካይ አይዳ አወል በበኩላቸው መተግበሪያው ወደ አገራቱ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ለሕገወጥ ደላሎች እንዳይጋለጡ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።  

መተግበሪያው የሕጋዊ ኤጀንሲዎችን ዝርዝር የያዘ መሆኑም ዜጎች በሐሰት መረጃ እንዳይታለሉ አዎንታዊ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።  

ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች የሚሄዱበት አገር ደመወዝ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን ያስረዱት ተወካይዋ፣ በአደጋ ወቅት የሚያገኟቸው ተቋማት መረጃም መካተቱን ጠቁመዋል።  

በተለይም የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችና የኢትዮጵያ ኮሙኒቲዎችን ማግኘት እንደሚያስችላቸው ነው ያስታወቁት።  

መተግበሪያው የሚሰሩባቸውን አገራት የውጭ ስምሪት ዓዋጆች መያዙም ዜጎች ችግር ቢገጥማቸው ራሳቸውን የሚከላከሉባቸውን መንገዶች እንዲያውቁ ይረዳል ነው ያሉት።  

ከጤና መረጃዎች ጋር በተያያዘም ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጨምሮ መረጃ እንደሚሰጥ ተወካይዋ አብራርተዋል።     

በመተግበሪያው በአገራቱ የሚገኙ የሥራ ዕድሎች መካተታቸውንም አክለዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ለውጭ አገራት በራቸውን ዘግተው የነበሩት ኳታር፣ ዮርዳኖስና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በቅርቡ ሠራተኞችን መቀበል መጀመራቸው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም