የኢትዮጵያና ኮትዲቯር አየር መንገዶች መንገደኞችን ለመቀባበል ተስማሙ

55
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኤር ኮትዲቯር መንገደኞችን ለመቀባበል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱ ከዚህ ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የአየር መንገዶቹ ደንበኞች በአንድ ቲኬት የጉዞ በረራ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። በሁለቱ አየር መንገዶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ የመዳረሻ በረራ አቅማቸውን ለማሳደግና በምዕራብ አፍሪካና በአሜሪካ የአየር መስመር የሚጓዙ ደንበኞችን ለማስተናገድ እንደሚያግዝ ተገልጿል። በስምምነቱ አማካኝነት ከምዕራብ አፍሪካ በተለይም ከጋና አክራ፣ ከቤኒን ኮቶኑ፣ ከቶጎ ሎሜና ከናይጄሪያ ሌጎስ ከተሞች የሚነሱ ተጓዦች በኤር ኮትዲቯር በረራ አድርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮትዲቯር ርዕሰ መዲና አቢጃን በማድረግ በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት ኔዋርክ ከተማ በሚያደርገው ቀጥታ በረራ በመገልገል ፈጣን ትስስር መፍጠር ይችላሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከእህትማማች የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር እንዲህ አይነት የትብብር ስምምነት ማድረግ በአፍሪካ አህጉር ያለውን የአየር በረራ መዳረሻ ክፍተት በመሙላት የዘርፉን የገበያ ድርሻ ለማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል። አየር መንገዱ በአቢጃን በማድረግ በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት የምትገኘው ኔዋርክ የሚያደርገው አዲስ በረራ ከቶጎ ርዕሰ መዲና ሎሜ ወደ ኔዋርክ ከሚያደርገው ጉዞ ጋር ተመጋጋቢ እንደሆነ ተናግረዋል። የኤር ኮትዲቯር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ሬኔ ዴኩሬ በበኩላቸው "ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ወዳጅነታችንን በማጠናከራችን ደስተኞች ነን” ብለዋል። ስምምነቱ የሁለቱ የአየር መንገዶች የረጅም ጊዜ ትብብር ጅማሮ እንደሆነና በበረራው አማካኝነት የአፍሪካ ተጓዦች በአውሮፓ አልፈው ወደ አሜሪካ እንዲጓዙ በማድረግ ሁለቱን አየር መንገዶች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ 58 እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ112 በላይ መዳረሻዎች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም