ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪካዊ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው-አምባሳደር ማይክል ራይነር

64
አዲስ አበባ ሀምሌ 12/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ አንስቶ ታሪካዊ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ተናገሩ። የአሜሪካ - ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ረይነር እንዳሉት በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ወሳኝና ታሪካዊ ነው። ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣንን በገዛ ፍቃድ መልቀቅ ጀምሮ ያሉትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ያደነቁት አምባሳደሩ አሁን እየታየ ያለው ፈጣን ለውጥ በኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ የመጣ ሲሉም ገልጸውታል። በተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችም ሰላምና መረጋጋት መስፈኑ፣ ሰብአዊ መብቶች መከበር መጀመራቸው፣ ሁሉን አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ የፖሊቲካ ስርዓት መታያቱና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስቀጠል የሚያስችሉ ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋልም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቶ ቀናት የስልጣን ቆይታቸው ያከናወኗቸው ስራዎችም በጣም ወሳኝና ትልቅ ለውጥ ያመጡ ናቸው ብለዋል። ይህ ለውጥና ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎች እንቅፋት ሊያገጥማቸው እንደሚችል የጠቆሙት አምባሳደሩ ሁሉም ለለውጡ የበኩልን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። ሰብዓዊ መብት የተረጋገጠባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካዔል በበኩላቸው ከዚህ በፊት ሲያጨቃጭቁን የነበሩ የሰብዓዊ መብት አያያዝና መሰል ችግሮች ዛሬ በቂ ትኩረት አግኝተው መልክ  እየያዙ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ በሁለቱ መንግስታት መካከል ያለውን መደጋገፍና መግባባት ያጎለብታል ብለዋል። በቀጣይ በአሜሪካ ከሚገኙ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መግባባትን ለማምጣት ተከታታይ ውይይቶች እንደሚያደረጉ አክለዋል። ከዚህም በፊትም የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን  ሲሰነዝር መክረሙ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም