ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ በጎንደር ከተማ በ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብተው አስመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ በጎንደር ከተማ በ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብተው አስመረቁ

ጎንደር፣ ህዳር 27/2013( ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነቧቸውን ሁለት ብሎክ የመማሪያ ህንጻዎች ዛሬ አስመረቁ፡፡
የመማሪያ ህንጻዎቹን ያስገነቡት ኢንጂነር አክሱማዊት አብርሃ የተባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ኢንጅነሯ በውጪ ሀገር የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማስተባበር በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ የመማሪያ ብሎኮቹን ገንብተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢንጅነሯ በመጪው የካቲት ወር 2013 ዓም በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማሪያ ህንጻዎችንና ቤተ-መጻህፍት በመገንባት ደረጃቸውን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል፡፡
የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አመት የ45 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል አቅዶ በአምስቱ የማስፋፊያ የግንባታ ስራ ተጀምሯል።
ኢንጅነሯ የተማሩበትን ትምህርት ቤት በማስታወስ ተነሳሽነቱን ወስደው የቀድሞ ተማሪዎችን በማስተባበር ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
የቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ምህረት ይመር "ኢንጅነሯ በእንጨትና ጭቃ የተሰሩ የመማሪያ ክፍሎችን ደረጃ በማሻሻል ለተማሪዎች ምቹ የትምህርት አካባቢ መፍጠር ችለዋል" ብለዋል።
የተገነቡት ሁለት ብሎክ የመማሪያ ህንጻዎች ባሏቸው ስምንት የመማሪያ ክፍሎች በአንድ ፈረቃ 400 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
በትምህርት ቤቱ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ዮርዳኖስ ሰለሞን ''በጭቃ የመማሪያ ክፍል ስንማር ወለሉ አቧራ በመሆኑ ለጉንፋን በሽታ እንጋለጥ ነበር'' ብላለች፡፡
''አዲሶቹ የመማሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን ጠብቀው የተሰሩ በመሆናቸው ለትምህርት አቀባበልና ለጤናችም ምቹ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ ደስታ ተሰምቶኛል'' ስትል ተናግራለች፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ቤቱ የህንጻ ግንባታ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የእውቅና ምሰክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን ለኢንጅነሯ ደግሞ የሰርተፊኬትና የካባ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በ1974 ዓም የተመሰረተው የጎንደር የቀይ አምባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ከሚገኙ አንጋፋ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው፡፡