በባሌ ዞን 5 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በቡና ችግኝ ተሸፍኗል

78
ጎባ ሐምሌ 12/2010 በባሌ ዞን አምስት ሺህ ሄክታር የሚጠጋ አዲስ መሬት በቡና ችግኝ ተሸፍኖ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ገለጸ። የባለስልጣኑ የቡና ልማት ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ነጋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት መሬቱ የተሸፈነው ውርጭና ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት በሚሰጡ ከ12 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ነው። በአሁኑ ወቅት በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች የሚገኙ 31 ሺህ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ለተተከሉት የቡና ችግኞች እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቡና ችግኞቹ በዞኑ በተቋቋሙ ከ6 ሺህ በሚበልጡ የመንግስትና የግል ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት። እንደባለሙያው ገለጻ የቡና ተከላ ሥራው የተከናወነው ከግንቦት ወር ጀምሮ እየጣለ ያለውን የክረምት ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም ነው። የቡና ዝርያዎቹ ከጅማና መቻራ የግብርና ምርምር ማዕከላት አዲስ የፈለቁትን "ሞካ " እና "ዴሱ" ን ጨምሮ 12 የአካባቢው ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። አዲሶቹ የቡና ዝርያዎች በሽታን በመቋቋም ከነባሩ ዝርያ በሄክታር ይገኝ የነበረውን 5 ኩንታል ወደ 12 ኩንታል የማሳደግ አቅም እንዳላቸው በሰርቶ ማሳያ ጣቢያዎች በሙከራ መረጋገጡንም አቶ ወንደሰን አመልክተዋል። በልማት ጣቢያ ሠራተኞች ለቡና ችግኝ የሚደረገው እንክብካቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱም ዓምና ከተተከሉት 18 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ውስጥ 85 በመቶ መጽደቁን ለአብነት ጠቅሰዋል። በቡና ልማት ከተሳተፉት መካከል የደሎ መና ወረዳ አርሶ አደር ከድር ኡሰማን በሰጡት አስተያየት በቡና ልማት የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም በምርጥ ዘር እጥረት ምክንያት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። በዘንድሮ ክረምት ከምርምር ማዕከላት ያገኙትን ሁለት አዳዲስ ዝርያ የቡና ችግኝ በመትክል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በአሁኑ ወቅት ተገቢ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ያረጁ የቡና ተክላቸውን በመጎንደል በአዲስ የቡና ዝርያ በመተካት ለተሻለ ውጤት እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አብዱሰላም ማህሙድ ናቸው። አርሶ አደር ሙስጠፋ ሁሴን "የገቢ ምንጬን ለማስፋት ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በቡና ልማት እየተሳተፍኩ ነው" ብለዋል። በባሌ ዞን ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ ሲሆን በየዓመቱም 15 ሺህ ቶን ተመርቶ ለገበያ ይቀርባል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም