ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ እዚህ ለመድረሷ የሴቶች ተጋድሎ ከፍተኛ ነው

105

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ ) ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ከሙሉ ክብሯ ጋር አሁን ላለችበት ደረጃ እንድትደርስ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጋድሎ ጉልህ መሆኑ ተነገረ። 

በአገሪቷ አሁናዊ ሁኔታም የሴቶች ተጋድሎ አንፀባራቂ ገድል እያስመዘገበ ይገኛል ተብሏል።

"የፀረ-ሴቶች ጥቃት ቀን"  በአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ አዘጋጅነት በመኮንኖች መኖሪያ ታስቦ ውሏል።

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በመርሃ ግብሩ ታድመዋል።

ቀኑ "ሠላምን በማረጋገጥ የሴቶችን ጥቃት እንከላከል፤ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጾታዊ ጥቃትን ባለመታገስ የብልጽግና ጉዞን እናረጋገጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የታሰበው።

በአገር መከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን የግንባታ ሰነዶች ዝግጅትና ስልጠና ስራዎች ዳይሬክተር ብርጋዴል ጄኔራል አስፋው ማመጫ "በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሴቶች ተሳትፎ ጉልህ ሲሆን አገሪቷም ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ከነሙሉ ክብሯ እዚህ እንድትደርስ የሴቶች ተጋድሎ ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

ይሁንና ስለ ሴቶች ያለው አሉታዊ አመለካከት ሊታረም የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በምድር ኃይል የጦር መምሪያ የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ኮሎኔል ሁሉአገርሽ ድረስ በበኩላቸው ሴት የሠራዊት አባላት በአገሪቷ አራቱም የዕዝ ማዕከላት የተሰጣቸውን ግዳጅ በመወጣት አንፀባራቂ ገድል እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ በተካሄዱ አውደ ውጊያዎች ሴቶች አኩሪ ተጋድሎ እየፈጸሙ መምጣታቸውን አስታውሰው ሠራዊቱ የተገነባበትን እሴት መላበሳቸው ደግሞ ለድላቸው ውጤት ግንባር ቀደሙን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጽህፈት ቤት ረዳት የዶክመንቴሽን ኦፊሰር ሻለቃ ዮርዳኖስ አሰፋም ሴት የሠራዊት አባላት መላው እናቶችና እህቶች ንጹህ የሠላም አየር የሚተነፍሱባትና ከስጋት ነጻ የሆነች ምድርን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማውረስ ዝግጁነታቸው እያሳዩ እንደሆነ ገልፀዋል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጀብድ በመፈጸም የባንዳውን ህወሓት የክፋት ሴራ በመበጣጠስ እየሰሩ ላሉት ጀግኒቶች ምስጋና አቅርበዋል።  

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንዔል በቀለ በበኩላቸው ማንኛውም ጾታን መሰረት አድርጎ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ ለተሰው የሠራዊት አባላት የህሊና ፀሎትና የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን የደም ልገሳም ተካሂዷል።

የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ29ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ15ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ ነው።

የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን አስመልክቶም ለ16 ቀናት የሚቆይ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም