የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ የገላና ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

86
ነገሌ ሐምሌ 12/2010 ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጋለጥና የአካባቢየቸውን ሰላም በመጠበቅ የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ በምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ በሀገሪቱና አካባቢያቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቶሬ ከተማ ተወያይተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ከተሳተፉት መካከል የወረዳው ቀርሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሩፎ ቢፍቱ በሰጡት አስተያየት በሰፈር አሉባልታ ህዝብ ከህዝብ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ አካላት በመካከላቸው ተሸሽገው መኖር እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ አሁን የተጀመረው የሰላምና የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ የጥፋት ኃይሎችን አጋልጠው ለመንግስት አሳልፈው በመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ በወረዳው የቶሬ ከተማ ነዋሪው  ወጣት አለማየሁ ዋሬ ካሁን በኋላ የጥፋት ኃይሎች ወጣቱን መጠቀሚያ የሚያደርጉበት እድል እንደማይኖር ተናግሯል፡፡ ወጣቱን መጠቀሚያ በማድረግ  የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር የሚንቀሰቅሱ አካላት አደብ ሊገዙ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ አካል በማጉደል፣ ንብረት በማቃጠልና መንገድ በመዝጋት በአካባቢያቸው ይደርስ  የነበረው ችግር እንዳይደገም መንግስት ከህዝብ ጋር በመተባበር ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ የአካባቢየቸውን ሰላም በመጠበቅ የሀገሪቱን የለውጥ  ጉዞ ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጿል፡፡ "በጥፋት ኃይሎች አሉባልታ በሚፈጠር ግጭት መጀመሪያ የሚጎዱት በተለይ ህጻናትና ሴቶች ናቸው " ያሉት ደግሞ ሌላዋ የውይይቱ ተሳታፊ  ወይዘሮ ተዋበች ዲላንቾ ናቸው፡፡ ታዳጊ ወጣት ልጆች የጥፋት ኃይሎች መጠሚያ እንዳይሆኑ ማስተማርና መምከር በመጀመሪያ የእናቶች ቀጥሎ የሀገር ሽማግሌዎችና የመንግስት ስራ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ በጌዲኦና በምዕራብ ጉጂ  ዞኖች  አዋሳኝ አካባቢ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ችግር በተለይ  በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመጥቀስም ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡ "መንግስት ማገዝ እንጂ ችግሩን ብቻውን መፍታት ስለማይችል የጥፋት ኃይሎችን  ከመካከላችን ለይተን በማውጣትና በማጋለጥ የመፍትሄውም አካል መሆን አለብን " ብለዋል ወይዘሮ ተዋበች፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የጥፋት ኃይሎች በፈጠሩት ችግር የተዘጉ የንግድ ባንክና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎች እንዲከፈቱም ጠይቀዋል፡፡ የውይይት መድረኩን የመሩት የዞኑ አስተዳደር ተወካይ  አቶ ተፈሪ ወንዳፈረው " የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከዳር የሚደርሰው ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር በመተጋገዝ በሙሉ አቅሙ ሲሰራ ነው፡፡ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለይቅርታ ቦታ በማይሰጡና ለውጡን በማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎች ላይ መንግስት እርምጃ ከመውሰድ እንደማይቆጠብም አስታውቀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ከአካባቢው ቀበሌዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች  ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም