የመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ ጀምሯል

81
አዲስ አበባ ሃምሌ 12/2010 የመቀሌ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ተተኪ ተጫዋቾችን ለማፍራትና የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ። የክለቡ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለኣከ ገብረህይወት ለኢዜአ እንደገለጹት ክለቡ ከሐምሌ 1 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ የገቢ ማሳባሰቢያ ስራ እያከናወነ ነው። ገቢውን ለማሰባሰብ ይረዳ ዘንድ 12 አባላት ያሉት አብይ ኮሚቴ መቋቋሙንና አምስት አባላት ያሉት አምስት ንዑሳን ኮሚቴዎች መደራጀታቸውን ተናግረዋል። የተቋቋመው ኮሚቴም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎች፣ በመቀሌ ከተማ ከሚኖሩ በተለያዩ የስራ መስኮች ከተሰማሩ ባለሃብቶችና ተቋማት ገቢ እንዲሚሰበስብ ገልጸዋል። ክለቡ የተለያዩ መጠይቆችን በመበተን ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት በጥሬ ገንዘብ፣ በአይነትና በስፖንሰር የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ለማዘጋጀት እቅድ መያዙንና በዚሁ የገቢ ማሰባበሰቢያ ላይ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል። መቀሌ ከተማ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ከራያ ቢራ አክሲዮን ማህበር ጋር የተፈራረመው ለሶስት ዓመት የሚቆይ የማልያ ስፖንሰርሺፕ ውል ክለቡ ራሱን በፋይናንስ ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት አካል እንደሆነ ነው አቶ ለኣከ ያስረዱት። በአጠቃላይ ለሁለት ወር በሚቆየው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም ጠቁመዋል። በሚገኘው ገቢም ዋናውን ቡድን የሚመግቡ ተተኪ ተጫዋቾችን የማፍራትና የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ስራ ለመግባት ጥረት እንደሚደረግም ነው አቶ ለኣከ የተናገሩት። መቀሌ ከተማ በየዓመቱ ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችን በመጠቀም አቅሙን እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል። የመቀሌ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ውሉ በመጠናቀቁ ከክለቡ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ነው። በዮሐንስ ሳህሌ ምትክ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ክለቡ ጥረት እያደረገ እንደሆነና በቅርብ ጊዜ ውስጥ አሰልጣኝ እንደሚሾም ገልጸዋል። ክለቡ ከዘንድሮው ዓመት በተሻለ መልኩ በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ለመሆን ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርምም አክለዋል። በ2010 ዓ.ም ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያደገው መቀሌ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ 49ኝ ነጥብ በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም