በጎንደር ከተማ ከ364 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

63

ጎንደር ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ከ364 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ገለጹ።

በከተማው እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ  የሚመክር ህዝባዊ መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ  የከተማ አስተዳደሩ የልማት አቅድ ዝግጅትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አስቻለው መልካሙ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ የከተማውን እድገት የሚያፋጥኑና የስራ እድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

ከልማት ፕሮጀክቶቹ መካከልም የመንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሟላት፣ የመንገድ ዳር መብራቶችን መዘርጋት፣ የወጣቶች መናፈሻ ፓርኮችና የጥቃቅንና አነስተኛ ሼዶች ግንባታ ይገኙበታል፡፡

በተለይም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ተደራሽ በማድረግ በኩል 14 ኪሎ ሜትር  የድንጋይ ንጣፍ ፣ስምንት  ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ከፈታ ስራና ስምንት መካከለኛ ድልድዮች ግንባታ ተጠቅሷል።

በ2012 የበጀት ዓመት ከ28ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል መመቻቸቱን ያወሱት ቡድን መሪው ዘንደሮ ደግሞ  ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በከተማዋ ባሉት የኢንቨሰትመንት አመራጮች መሳተፍ የሚፈልጉ 170  ባለሀብቶች  ለማስተናገድ መታቀዱን ጠቁመው ወደ ኢንደስትሪ መንደሮች የሚያስገባ የሁለት ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በህወሃት ጁንታ ላይ በተወሰደው የህግ  ማስከበር እርምጃ  የተመዘገበውን ድል በልማቱም ለመድገም ከተማ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል፡፡

በልማት ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን የአፈጻጸም መጓተትና የጥራት ችግር ፈትሾና ገምግሞ የህዝቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ  ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ተወካዮች   ከጊዜ ወደ ጊዜ በከተማዋ የሰፈነ  የመጣው  ሰላም ለኢንቨስትመንት ፣ቱሪዝምና ንግድ  እንቅስቃሴ ምቹ   እንዳደረገው   መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

በሚካሄዱ የልማት ስራዎች ላይም ህብረተሰቡን በማስተባበር በገንዘብ ፣እውቀትና  ጉልበት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም