የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በአሽከርካሪዎች ስነ-ምግባር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ

145

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ በአሽከርካሪዎች ሰነ-ምግባርና በመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን በአዲስ አበባ አቤት ሆስፒታል አዘጋጅነት በዛሬው እለት ተከብሯል።

እለቱን በማስመልከት በትራፊክ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በሰፍራው በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም የትራፊክ አደጋ እኛን ለብዙ ችግርና ስቃይ ዳርጎናል፤ በቀጣይ አደጋ እንዲቀንስ ለማስቻል በአሽከርካሪዎች ሰነ-ምግባርና መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስገልጋል ብለዋል።

ከተጎጂዎቹ መካከል አቶ ደስታ ገብረመድህን፤ ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም በመንገድ ላይ እየተጓዙ ከፍጥነት በላይ በሚነዳ አሽከርካሪ ተገጭተው ለከፍተኛ  የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ተጎጂ የከባድ መኪና ሹፌር ጥላሁን ዘነበ፣ ወደ ድሬደዋ በሚጓዝበት ወቅት መስመሩን በሳተ ተሸከርካሪ ተገጭቶ ለከፋ የአካል ጉዳት መዳረጉን ተናግሯል።

በዚህ አጋጣሚ የሚያሽከረክረው መኪና ረዳት ሕይወቱ ማለፉን አስታውሷል።

የትራፊክ አደጋ ጉዳት በተጎጂው ብቻ የሚቀር አለመሆኑን የተናገረው ጥላሁን በተለይ የሹፌሮች ጥንቃቄ አደጋውን ከመቀነስ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

የአቤት ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ከፈለኝ፣ ሆስፒታላቸው በ2012 ዓ.ም. ህክምና ከሰጣቸው የድንገተኛ አደጋ ህሙማን መካከል ከ65 በመቶ በላይ የመኪና አደጋ ተጎጂዎች መሆናቸውን አስታውሰዋል።

በትራንስፖርት ሚኒስትር የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ፈቲያ ደድገባ "የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን" የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ይህን አደጋ ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘንደሮው ሩብ ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ 929 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ሲያልፍ 1 ሺህ 382 ሰዎች ከባድ እንዲሁም 1 ሺህ 130 ሰዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት እነደደረሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዓለም አቀፍ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን በዓለም ለ15ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም