የኢትዮጵያን ዲጂታል ሪፎርም ትግበራ ፕሮጀክት የሚያግዝ የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተደረገ

67

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን መካከል የኢትዮጵያን ዲጂታል ሪፎርም ትግበራ ፕሮጀክት የሚያግዝ የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ተደረገ።

ስምምነቱን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ባዩ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ቡድን መሪ ሳነ ዊለምስ ናቸው ዛሬ የፈረሙት።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን የንግድ ሥራ ቅልጥፍና ለማሻሻል የተነደፈውን ፕሮግራም የሚያግዝ ሲሆን የዲጂታል ሪፎርም ፕሮጀክትን እንደሚደግፍም ተገልጿል።

ለአንድ ዓመት ለሚቆየው ለእዚህ ፕሮጀክት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን  የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንደሚያደርግና ፕሮጀክቱም ከታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንደሚቆይ ታውቋል።

የገንዘብ ድጋፉ ድሬዳዋና ባህር ዳር ከተሞችን የብሔራዊ የንግድ ፖርታል አካል ለማድረግ እንደሚውልም ተጠቁሟል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ባዩ እንዳሉት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ቅልጥፍና ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ የሆነው የንግድ ሥራ ቅልጥፍናን ማሻሻል ሥራ የሚያከናውንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ በ2011 ዓ.ም ተቋቋሙ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

ዶክተር አብዮት እንዳሉት፣ ኮሚቴው ለንግድ ሥራ ቅልጥፍና ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን የመፍታት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዲጂታል ዘርፉ የሚከናወነው ሥራም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራ ነው።

የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ያደረገው ድጋፍም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዲጂታል ዘርፍ የተጀመረውን የንግድ ሥራ ቅልጥፍና ማሻሻልና የዲጂታል ማሻሻያ ትግበራን ያግዛል ብለዋል።

በአሜሪካው የፋይናንስ አገልግሎት ተቋም ማስተር ካርድ ድጋፍ አማካኝነት በ2012 ዓ.ም አዲስ አበባን ብሔራዊ የንግድ ፖርታል አካል የማድረግ ሥራ ተከናውኗል።

አውሮፓ ህብረት በሚያደርገው ድጋፍም ባህር ዳር እና ድሬዳዋ ከተሞችን የንግድ ፖርታሉ አካል የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

"በተጨማሪም ድጋፉ የንግድ ስራዎችና አገልግቶች በቴክኖሎጂ የተደገፉ ለማድረግ ለሚሰሩ ሥራዎች ይውላል" ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ተግባራዊ እያደረገች እንደሚገኝና ይሄም ለኢኮኖሚ እድገቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው አክለዋል።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ቡድን መሪ  ሚስ ሳነ ዊለምስ "ስምምነቱ ሕብረቱ ኢትዮጵያን የጀመረችውን የዲጂታል ማሻሻያና የአገር በቀል ኢኮኖሚ አጀንዳ የመደገፍ አካል ነው" ብለዋል።

በኢኮኖሚ አጀንዳው የግሉ ዘርፍ ዋንኛውን ድርሻ እንዲወስድ የተያዘውን ግብ የአውሮፓ ሕብረት እንደሚያበረታታውና አጀንዳው ለሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት የግሉ ዘርፍ ሚና አለው ከሚለው የሕብረቱ ስትራቴጂ ጋር የሚሄድ እንደሆነ ገልጸዋል።

"ዲጂታላይዜሽንና የኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር (ኢ-ጋቨርናንስ) ስርአቶች የንግድ ስርአቱ ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ" ብለዋል።

"ዲጂታላይዜሽን ማህብራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያፋጥን ነው" ያሉት ሚስ ሳነ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለውን ትስስር እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ማሻሻያ ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም