በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

59

ጋምቤላ ህዳር 24 / 2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

"ኤች አይ ቪን ለመግታት አለም አቀፋዊ ትብብር የጋራ ኃላፊነት"   መሪ ሀሳብ 33ኛው የዓለም የጸረ ኤድስ ቀን በክልል ደረጃ ዛሬ  በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ቶማስ ቱት በወቅተ እንደተናገሩት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤች አይ ቪ /ኤደስ ቫይረስ ስርጭት   እየቀነሰ  ቢሆንም በክልሉ  አሁንም  ጨምሯል።

ቫይረሱ በተለይም በአምራቹ ዜጋ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል አደለም ብለዋል።

የቫይረሱን የስርጭት ለመግታት የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ብርቱ ሥራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮድ ጋርዊች በበኩላቸው በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩን በማጠናከር በተለይም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል   ጥረት  ሲደረግ  መቆየቱን ተናግረዋል።

ሆኖም የተደረገው ጥረት በተፈለው ልክ ውጤት እንዳለተገኘ ጠቁመው የኤክስቴንሽን መረሃ ግብሩን በማጠናክር  የተሻለ ውጤት ለማምጣት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኘየል እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት ቢቀንስም  በክልሉ ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ  ነው።

ለዚህም ማሳያው በሀገር አቀፍ ደረጃ የቫይረሱ ስርጭት መጠን 0 ነጥብ 93 በመቶ ሲሆን የክልሉ የስርጭት መጠን 4 ነጥብ 7 ከመቶ መሆኑ ነው ሲሉ አመላክተዋል።

በክልሉ የሚገኙ የመንግስታዊም ሆኑ የግል ተቋማት የቫይረሱን ስርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን ከመደበኛ እቅዳቸው ጋር አካተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጽህፈት ቤቱ  የስርጭቱነ  መጠን ለመቀነስ፣ የጤና  አገልግሎትን ተደራሽ ለማደረግና የዘርፉ ሌሎች ግቦችን ለማሳካት ስትራቴካዊ እቅድ  በማዘጋጀት እየሰራ  እንሚገኝ  ጠቁመው  ለስኬቱ የሁሉም ድጋፍና  ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጋምቤላ የጸረ ኤድስ ቀን ሻማ በማብራት ፣ የደም ምርመራ፣ የምክር አገልግሎትና  ሌሎች ግንዛቤን በሚያሳድጉ ዝግጅቶች   ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም