ከሃዲውን ኮሎኔል ማንቁርቱን ይዛ ያስረከበችው ጀግና ምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ

113

አዲስ አበባ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) ጀግናዋ ም/አስር አለቃ ከሀዲውን ኮሎኔል ማንቁርቱን ይዛ አስረከበች ።

የሰሜን ዕዝ ካሉት ክፍለ የጦሮች መካከል 20ኛ ቃሉ ክፍለ ጦር አንዱ ነው። 

ክፍለ ጦሩ በዕዙ እንዳሉት ሌሎች ክፍለ ጦሮች ሁሉ በጽንፈኛው የህወሓት ጁንታ የክህደት ጥቃት ተፈጽሞበታል።

በዚህ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አባል የሆነችው ምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገብረዮሐንስ አጃቢ ነች ።

ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ጽንፈኛው ቡድን በቀጣይ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳፋሪ የሆነ የክህደት ጥቃት መፈጸሙን ትናገራለች።

"ጥቃቱ የተፈፀመው ሠራዊቱ በተኛበት መሆኑ ደግሞ ድርጊቱን ይበልጥ አሳዛኝ ያደርገዋል" ነው ያለችው።

ምክትል አስር አለቃ ገበያነሽ ከጥቃቱ ቀደም ብሎ የሻለቃው አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገብረዮሐንስ ከጽንፈኛው ቡድን ሲቪል አመራሮች ጋር በተደጋጋሚ ይገናኝ እንደነበረ ነው የገለጸችው።

ኮሎኔሉ የህወሓት የእብሪት እርምጃ ከመጀመሩ ከሦስት ቀናት በፊት ሠራዊቱ የምግብና መጠጥ አገልግሎት የሚያገኝባቸውን መንገዶች በመዝጋት ሠራዊቱን ለከፍተኛ ረሃብና ጥም ዳርጓል።

ሁሉም የሠራዊት አባል የግል ትጥቁን በአንድ ክፍል በማስቀመጥ በኅብረተሰብ የድጋፍ ሥራዎች ላይ እንዲረባረብ ማድረጉንም ትናገራለች ።

ነገር ግን ኮሎኔል ሰለሞን በውጭ ካሉ ሲቪል አመራሮች ጋር በመነጋገር በሠራዊቱ ላይ እየሰራ ያለውን ደባ ጠንቅቄ ስለማውቅ በንቃት ስትከታተለው ነበር ብላለች።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ሁሉም የጥበቃ ቦታዎች በትግራይ ተወላጅ የሠራዊት አባላት እንዲሸፈኑ በማድረግ የከሃዲው ቡድን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በ13 መኪናዎች ሻለቃውን መክበቡን ታስታውሳለች።

ሠራዊቱ ምንም ሳይዘጋጅ በድንገት ከፍተኛ ተኩስ እንደከፈቱበት ነው ምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ የምትገልጸው።

"ሆኖም ሠራዊቱ በታላቅ ጀግንነት የማይታሰቡ ጀብዱዎች ጭምር በመፈፀምና ወደ ኤርትራ ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ ራሱን ማዳን ችሏል" ብላለች።

በዚህ ሁሉ ግፍና በደል መሃል ሠራዊቱን የከዳው የሻለቃዋ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሰለሞን ገብረዮሐንስ መፀዳጃ ቤት ውስጥ በመደበቅ በጁንታው የተሰጠውን ተልዕኮ ሲያስፈጽም እንደደረሰችበት ትናገራለች።

እናም ኮሎኔሉ 'ከተደበቀበት መፀዳጃ ቤት እንዲወጣና እኔ የምለውን ብቻ እንዲፈፅም፤ እሺ የማይል ከሆነ ግን እርምጃ እንደምወስድበት አስጠነቀቅኩት" ትላለች።

በፍርሃት ውስጥ ሆኖ የታዘዘውን መፈጸም መጀመሩን፤ ለመሮጥ ሲሞከር እየተኮሰች ተከትላ ከሁለት ጓዶቿ ጋር በመሆን በማስቆም ሽጉጥና ማዕረጉን መቀበሏን፤ ጫማውን አስወልቃ ሌሊቱን በእግር ጉዞ ኤርትራ ይዛው መግባቷን ለኢዜአ ሪፖርተር ተርካለች።

ከሃዲውን ኮሎኔል ኤርትራ እንደደረሰች ለሚመለከተው አካል አሳልፋ እንደሰጠች እንዲህ አብራርታለች።

ከሃዲውን ኮሎኔል ይዛ ወደ ኤርትራ ለመሻገር የወሰነችው መረጃው ለቀጣይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚጠቅም በማመኗ መሆኑንም ገልፃለች።

መከላከያ ሠራዊቱ በራሱ ወገኖች የደረሰበትን በቃላት የማይገለፅ ግፍና በደል ተሸክሞ ቂም ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ፍቅር አስቀድሞ ለድል በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማትም ምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ተናግራለች።

የምክትል አሥር አለቃ ገበያነሽ ደባልቄ ታሪክ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ከሕይወታቸው ይልቅ የሕዝባቸውን ደህንነት የሚያስቀድሙ የበርካታ ጀግኖች እናት መሆኗን አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም