በጃካርታ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢንዶኔዥያ የሚዲያ ተቋማት በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጠ

63

አዲስ አበባ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በጃካርታ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ መንግሥት በትግራይ ክልል ህግና ሥርዓትን ለማስከበር የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ በኢንዶኔዥያ ለአራት የሚዲያ ተቋማት ማብራሪያ ሰጠ፡፡

በጃካርታ የኢፌዴሪ አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ ሰሞኑን ለመንደይ ሚዲያ የተባለ የሚዲያ ግሩፕ ሥር  ለሚገኙ አራት የሚዲያ ተቋማት መንገስት በትግራይ ክልል ስላካሄደው የሕግ ማስከበር ተግባር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በመግለጫቸው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ስራ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሕገ-መንግሥቱን የማስከበርና የአገርን ህልውና የማስቀጠል ዓላማ እንዳለው አብራርተዋል። 

መንግሥት ሕግ ለማስከበር የተገደደው የህወሃት ጁንታ የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊትን በማጥቃት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመዝረፉና አገሪቷን አደጋ ላይ በመጣሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

አገሪቱን ለ27 ዓመታት በበላይነት ሲያስተዳድር የቆየው የህወሃት ቡድን የአገሪቱን ህግ፣ ሥርዓትና የማዕከላዊ መንግሥትን ትዕዛዝ ሲጥስ መቆየቱንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ምርጫ የተራዘመበትን ውሳኔ በመቃወም ከህገ-መንግስቱ ውጭ ቡድኑ የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ምርጫ ስለማካሄዱም ለሚዲያዎቹ ገልጸውላቸዋል።

የህወሃት ቡድን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ የብዙ ዜጎች ህይወት እንዲያልፍ፣ እንዲፈናቀሉና አገሪቱ እንዳትረጋጋ ሲሰራ መቆየቱንም አስረድተዋል።

የህወሃት ቡድን ያደራጀው ታጣቂ ሃይል በቅርቡ በማይካድራ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ መፈጸሙንም አምባሳደር አድማሱ አብራርተዋል።

በመሆኑም ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋትና የአገር ህልውና ለመታደግ ሲባል መንግስት ህግ የማስከበር አርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል። 

ኢንዶኔዥያ ከ267 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር ሆና በህዝብ ብዛት ዓለም በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ባህሳ ቢሆንም ከ700 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገርባታል።

የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ በደቡብ ምስራቅ እስያ በተለይም በማሌዥያና በሲንጋፖር በስፋት እንደሚነገር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በመሆኑም አምባሳደር ፕሮፌሰር አድማሱ ጸጋዬ የሰጡት ማብራሪያ የሚዲያ ተቋማቱ የሚጠቀሙበት ቋንቋ ሰፊ የሕዝብ ተደራሽነት ስላለው ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ኤምባሲው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም