ቻይና በሚሊዮን የሚቆጠር የኮቪድ-19 ክትባት ለዓለም እንደምትሰጥ አስታወቀች

56

አዲስ አበባ፤ ህዳር 23/2013(ኢዜአ) ቻይና በሚሊዮን የሚቆጠር የኮቪድ-19 ክትባት ለዓለም አገራት ለመስጠት ቃል ገባች። 

ክትባቱ ለስርጭት መዘጋጀቱ የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ክትባቱን ወደ ተለያዩ አገራት ከሚያጓጉዙ አየር መንገዶች አንዱ እንደሆነም ተነግሯል። 

የኮቪድ-19 ክትባቱን ቅድሚያ ለማግኘት ቃል የተገባላቸው በማደግ ላይ ያሉ አገራት ቁጥር እየጨመረ መሆኑም ተጠቁሟል።

ቻይና የመጨረሻ የሙከራ ደረጃቸውን ያጠናቀቁ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ክትባቶችን ከቀጣዮቹ ወራት ጀምሮ ለዓለም አገሮች 'አሰራጫለሁ' ማለቷን ሲ.ኤን.ኤን በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ክትባቱን ከቻይና የሎጂስቲክስ ድርጅት ጋር በጥምረት ከሚያሰራጩ አየር መንገዶች መካከል መሆኑንም ዘገባው አክሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመካከለኛው ምስራቅና ለአፍሪካ አገራት ክትባቶቹን እንደሚያጓጉዝ ነው የተገለጸው።

አየር መንገዱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ መስፋፋቱን ተከትሎ ከ3 ሺህ ቶን በላይ የሕክምና ቁሳቁስ ለአውሮፓ፣ ለአፍሪካ፣ ለመካከለኛው ምስራቅና ለደቡብ አሜሪካ ሲያሰራጭ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል።

እንደ ሲ.ኤን.ኤን ዘገባ ቻይና ክትባቱን ማሰራጨቷ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀስን ተከትሎ በተሳሳተ አረዳድ የጠፋውን ገጽታዋን ለመመለስ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርላታል።

መነሻውን ቻይና ያደረገውና እስካሁን ፈዋሽ መድኃኒት ያልተገኘለት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለያዩ የዓለም አገራት ተሰራጭቶ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል።

ለወረርሽኙ ክትባት ለማግኘት የዓለም አገራት በጋራና በተናጠል እየሰሩ ሲሆን የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ካሰወቁት መካከል ቻይና፣ ሩሲያ፣ አሜሪካና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም