በደቡብ ክልል ስፖርታዊ ውድድሮች ሠላምና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እንዲያጠናክሩ ለማስቻል እየተሰራ ነው

67

ሀዋሳ፣ ህዳር 23 /2013 (ኢዜአ) ስፖርታዊ ውድድሮች ሠላምና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እንዲያጠናክሩ በሚያስችል መልኩ አደረጃጀቶችን  ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ገለጹ።


የኮሚሽኑ ልዩ ልዩ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በክልሉ ስፖርት ኮሚሽን የአደረጃጀትና ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ወንበሬ በጉባኤው መድረክ እንዳሉት በክልሉ የስፖርት ዘርፉን  በሰው ሃይልና ግብአት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ተከታታይነት ያለው የሙያ፣ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ትኩረት እንደሚሻ ያነሱት አቶ ሞገስ የስፖርት ልማቱ እንዲጎለብት ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስፖርታዊ ውድድሮች ሠላምና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ ዜጎች በስፖርት ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት አደረጃጀቶች ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተዋረድ የሚገኙ ፌዴሬሸኖች ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት ውድድሮችን ማካሄድና መልካም ስነ ምግባር ያላቸው ስፖርተኞችን ለማፍራትና ህዝባዊ ድጋፍ እንዲጎለብት ይደረጋል ብለዋል።

በጉባኤው የ2012 ዓም የውድድር ዘመን የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የተያዘው በጀት ዓመት ዕቅዶች ዙሪያ የሚመክር ሲሆን የስራ ዘመናቸውን ባጠናቀቁ፣ በተጓደሉ አባላትና የስራ ሃላፊዎች ምትክ ምርጫ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡

የእግር ኳስ፣ ቦሊቦል እና አትሌትክስን ጨምሮ የክልሉ ልዩ ልዩ  ስፖርት ፌዴሬሽኖች በጉባኤው እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም