በሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ልምምዱን ዛሬ በሩዋንዳ አድርጓል

64
አዲስ አበባ አምሌ 11/2010 በሩዋንዳ የሚካሄደው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ነገ ይጀመራል። በአገሪቷ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በሚካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አዘጋጇ ሩዋንዳ ፣ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ኬንያ ይሳተፋሉ። በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችና ሌሎች 10 ልዑካንን በመያዝ ትናንት ወደ ሩዋንዳ በማምራት ማምሻውን የአገሪቷ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ መድረሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በሰላም ዘርአይ አሰልጣኝነት የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ የመጀመሪያ ልምምዱን ማድረጉም ተገልጿል። ሉሲዎቹ ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የውድድሩን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ከኡጋንዳ ጋር በሩዋንዳ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰዓት ከኡጋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። ነገ በውድድሩ መክፈቻ ቀን በሩዋንዳ ብሔራዊ ስታዲየም ከቀኑ 8 ሰዓት ኬንያ ከኡጋንዳ፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ከ15 ደቂቃ አዘጋጇ ሩዋንዳ ከታንዛንያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በአጠቃላይ አምስቱ አገራት እርስ በእርስ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ እንደሚሆን የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) አስታውቋል። የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ወጪ በተቀመጠለት ጊዜ ለአዘጋጇ ሩዋንዳ ባለመላኩ ውድድሩ ከግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ  ሲራዘም ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የዘንድሮው ውድድር የመካሄድ ጉዳዩ አጠራጣሪ ሆኖ ቆይቶ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን ሴካፋ ለሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  የሚያስፈልገውን በጀት በመልቀቁ ምክንያት ውድድሩ የሚካሄድ ይሆናል። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የተለያዩ የአፍሪካ የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች ውድድር ለማስተናገድ የፋይናንስ ችግር በስፋት ሲገጥመው ይስተዋላል። ከሁለት ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኋላ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በበጀት ማጣት ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል። የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዛንዚባር ውድድሩን ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር ታንዛንያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎች አዘጋጇ ኡጋንዳን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁበት ከፍተኛ ያስመዘገቡት ውጤታቸው ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም