ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፉ

73

አዲስ አበባ ህዳር 19/2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፉ።

በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት እንዳሉት ''እነሆ ዛሬ! በሀገር መከላከያ ሰራዊታችን በሳል የውጊያ ጥበብ እና የትግል ወኔ የህውሃት ጁንታ ቡድን የከተመባትን የመቀሌ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል''።

በክልሉ መንግሥት በጥንቃቄ እና በፍጥነት እየወሰደ የሚገኘው ህግ የማስከበር እርምጃ በስኬት ታጅቦ ወሳኝ የድል ምዕራፍ ተቀዳጅቷል ነው ያሉት ።

ለዚህ ዘመን ተሻጋሪ ድል ላበቁን ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ለአማራ ክልል ልዩ ሃይል እና ሚሊሻዎች ታላቅ ምስጋና እና ክብር ይገባቸዋል ብለዋል።

በህግ የማስከበር እርምጃ በኢትዮጵያዊነት ለአፍታ ለማይደራደረው የትግራይ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊቱ ብርቱ ደጀን በመሆን ለተጫወተው ታሪካዊ ሚና ልዩ ክብር እና ምስጋና ይገባዋል ሲሉም አመስግነዋል።

የጁንታውን ቡድን አድኖ ለህግ የማቅረብ ተልዕኮ የተቀጣጠለው የድል ስሜት እስከመጨረሻዋ ሰዓት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

መንግሥት በደረሰበት ወሳኝ የድል ምዕራፍ ዜጎችን ከጥቃት የመጠበቅ እና የመከላከል ተግባሩን በጥንቃቄ፣ በንቃት እና በሃላፊነት ስሜት የሚወጣም እንደሚሆንም ገልፀዋል።

በትግራይ ክልል እና በአካባቢው ፍፁም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግ ነው ያመለከቱት።

በአጭር ጊዜ በትግራይ ክልል በጁንታው ቡድን ሴራ የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት እና የማቋቋም እንዲሁም በሂደት በክልሉ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የማረጋገጥ ስራዎች በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል።

በጠንካራ የአመራር ጥበብ የተመራው ህግ የማስከበር እርምጃችን መሪ ዓላማ የጁንታውን ቡድን ካለበት ለቅሞ ለህግ የማቅረብ ተልዕኮ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አሁንም የትግራይ ህዝብ ወንጀለኞችን ከተደበቁበት ፈልፍሎ የማጋለጥ ታሪካዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም