ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ያቋቋመው የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማዕከል ስራ ጀመረ

57

ዲላ፣ ህዳር 19/2013( ኢዜአ) ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከኮሮና ጋር ተያይዞ በቀን ከአንድ ሺህ 200 በላይ ናሙናዎችን መመርመር የሚችል ማዕከል አቋቁሞ ስራ ጀመረ።

የምርመራው ስራ መጀመሩን በምረቃ ሥነ-ሥርዓት ይፋ በተደረገበት ወቅት በዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ መምህር አሰፋ አስናቀው በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ ለኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ቢሆንም ሌሎችንም በሽታዎች ለመመርመር የሚያስችል አቅም ያለው ነው።

በቀን በአማካይ ከ1ሺህ 200 በላይ ናሙናዎችን መመርመር የሚያስችለው ይህ ማዕከል በተጓዳኝ ለጤና ተማሪዎች የተግባር ልምምድ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

የኮሮና ምርመራ ማዕከሉ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎቱን በቅርበት መስጠት እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ ናቸው።

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ይህን ጥረት ለማገዝ ህብረተሰቡ ምልክቱ ታይቶብኛል ብሎ ባሰበበት ወቅት ምርመራ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቫይረሱ መያዛቸው የሚገመቱ ሰዎችን ማቆያና ማከሚያ ማዕከል በማቋቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ አስታውሰው ቀደም ሲል የምርምራ አገልግሎት  ባለመኖሩ ናሙና ተልኮ ውጤት እስኪደርስ ጫና እንደነበረና አሁን አገልግሎቱ በመጀመሩ ችግሩን እንደሚያስቀር ጠቁመዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ጉሻ ባላኮ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ያደርገው የነበረው ጥንቃቄ በተቀዛቀዘበት ወቅት  ማዕከሉ ስራ መጀመሩ መነቃቃትን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

የቫይረሱ መከላከያ ክትባት ቢገኝ ተጋላጭነትን ለይቶ ለመከተብ የማዕከሉ ስራ መጀመር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም