ሰራዊቱ መቀሌን እና የወንጀለኛው ጁንታ ቡድን አባላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ቦታዎችን ያዘ

67

አዲስ አበባ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌን እና የወንጀለኛው ጁንታ ቡድን አባላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂክ ቦታዎች መያዙን አስታወቀ። የትግራይ ህዝብ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ ለመከላከያ ሰራዊት ወገንተኝነቱን አሳይቷል። 

የአገር መከላከያ ሰራዊት ሀውዜን፣ አል ነጃሺ፣ አዲቀየህ፣ ማይመሳኖን እና ውቅሮን ከጁንታው ታጣቂ ሃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አድርጓል።

የህወሃት ጁንታ በሰላም እጁን እንዲሰጥ መንግስት የሰጠውን የ72 ሰዓታት ጊዜ ሊጠቀም ባለመቻሉ ከትናንት ጀምሮ የህግ ማስከበር ስራው ቀጥሏል።

በመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ የህግ ማስከበር ሂደት በውጤታማነት ቀጥሎ ተጨማሪ የትግራይ ክልል ከተሞችን ከጁንታው ታጣቂ ነፃ ማድረግ ተችሏል።

በዚህም በአድዋ ግንባር የተንቀሳቀሰው ሰራዊት ሃውዜን፣ አብርሃ ወአፅበሃንና ውቅሮን የተቆጣጠረ ሲሆን  አጉላን በግማሽ ቀን መቆጣጠሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በመቀሌ አቅራቢያ ወደሚገኘው መሰቦ ተራራ እየገሰገሰ ሲሆን ይህም መቀሌን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ግንባርም በአዲግራት በኩል ሳንቀጣ እና አልነጃሺን በመቆጣጠር ውቅሮ ገብቷል።

በሶስተኛው የራያ ግንባር ደግሞ አዲቀይህን የተቆጣጠረ ሲሆን ሄዋናና በመቆጣጠር ሁሉንም ምሽጎች ሰባብሮ ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛል።

በመቀሌ ያለውን የወንጀለኛ ቡድን የመቆጣጠር ተግባር በማጠቃላይ ምዕራፍነት የተያዘ ሲሆን ሰራዊቱ ግዳጁን በምን አኳኋን መፈጸም እንዳለበት በቂ ዝግጅት አድርጎ የወንጀለኛውን ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ የጁንታውን አባላት ለመያዝ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመከላከያ ሰራዊቱ በተግባር ወገንተኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።

የጁንታው ቡድን በፕሮፓጋንዳ ጭምር እያፈገፈገ መሄዱ ሽንፈቱን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም