በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሕንድና የባንግላዴሽ ባለሀብቶች ስለ ሕግ ማስከበር እርምጃው ገለጻ ተደርጎላቸዋል…አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ

474

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላላቸው የሕንድና የባንግላዴሽ ባለሀብቶች በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ማብራሪያ መሰጠቱን በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

ግብርና፣ የአበባ እርሻ ልማት፣ መድሐኒት ማምረቻ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የሕንድ ኩባንያዎች በዋነኝነት በኢትዮጵያ የተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ናቸው።

ኢትዮጵያና ባንግላዴሽም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ትብብር እያደገ የመጣ  ሲሆን፤ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች በዋናነት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስኮች በኢትዮጵያ ተሰማርተዋል።

ከኩባንያዎቹ አንዱ ዲቢኤል ግሩፕ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ተመርቆ በተከፈተው የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ ሲሆን ምርቶቹን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይልካል፤ ለኢትዮጵያዊያንም የስራ ዕድል ፈጥሯል።

በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ትዝታ ሙሉጌታ (ዶ/ር) በኒው ዴልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሕግ ማስከበር እርምጃው ዙሪያ በኢትዮጵያ መዋዕለነዋያቸውን ለሚያወጡ የሕንድና የባንግላዴሽ ኩባንያዎች ባለሀብቶች ገለጻ መደረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለሕንድ መንግስት፣ ኤምባሲው ለሚሸፍናቸው የባንግላዴሽ፣ ስሪላንካና ኔፓል አገራት የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም ስለ ሕግ ማስከበር እርምጃው ማብራሪያ መሰጠቱንም አምባሳደሯ ጠቁመዋል።

የሕንድ መንግስት የእርምጃውን ዓላማና ይዘት በግልጽ መገንዘቡንም ተናግረዋል።

በሕንድ የሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ አባል አገራት አምባሳደሮችን ጨምሮ በአገሪቷ ለሚገኙ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የማስረዳት ስራ መከናወኑንም ነው የገለጹት።  

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሕግ ማስከበር እርምጃው ዙሪያ የተሳሳተ አቋም እንዳይዝ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት እውነታውን እንዲረዳ ተደርጓል ነው ያሉት አምባሳደሯ።

በሕንድ ለሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ እየተሰጠ እንደሚገኝና ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ዘገባ  እያቀረቡ መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በጤናና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሲሆኑ፤ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ584 በላይ የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመስራት ፈቃድ መውሰዳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።