በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሰራ "ፕሮ-አግሮ ኢትዮጵያ" የተባለ ፕሮጀክት በሁለት ክልሎች ስራ ሊጀምር ነው

73

አዲስ አበባ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) በግብርናው ዘርፍ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚሰራ "ፕሮ-አግሮ ኢትዮጵያ" የተባለ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ስራ ሊጀምር ነው።

የዓለም ሥራ ድርጅት (አይ.ኤል.ኦ) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አሌክሲዩ ሙሲንዶ፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ለፕሮጀክቱ ክንውን ዛሬ የስምምነት ፊርማ አድርገዋል።

ፕሮጀክቱ 5 ሚሊዮን ዮሮ የተመደበለት ሲሆን በአማራና ደቡብ ክልሎች ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ይተገበራል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ፕሮጀክቱ መንግስት ምርታማነትን ለማሳደግና ስራ አጥነትን ለመቀነስ እያከናወነ ላለው ተግባር አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም ከጀርመን ሠራተኛ ሚኒስትር ጋር በተደረገው ውይይት በሙያ ደህንነት ጤናማነት፣ በህፃናት ጉልበት ብዝበዛና በግብርናው ዘርፍ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ምክክር መደረጉን አስታውሰዋል።

ዛሬ ስምምነት የተደረገበት ፕሮጀክትም በግብርናው ዘርፍ ምቹ የሥራ ሁኔታና በርካታ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ ከአገሪቱ ከ80 በመቶው በላይ ህዝበ የሚተዳደርበት  የግብርናው ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አስካሁን ባለው አፈፃፀም ወደ ውጭ ከተላኩት ግብርና ምርት 64 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል።

ሆኖም የግብርና ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው እየተላኩ ባለመሆኑ የሚሸጡበት ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ለማሻሻል አራት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፣ ሁለቱ ፓርኮች በከፊል ወደ ስራ በመግባት ወደ ውጭ ከላኳቸው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም አስረድተዋል።

በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በርካታ አርሶ አደሮች ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ጠቁመዋል።

በዛሬው ስምምነት የምርት አቅርቦትና መሰል ችግሮችን በመፍታት ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የዓለም ሥራ ድርጅት (አይ.ኤል.ኦ) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አሌክሲዩ ሙሲንዶ፤ ፕሮ-አግሮ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና በሞሮኮ እንደሚተገበርና ለእያንዳንዳቸውም 5 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በግብርናው ዘርፍ ምቹ ሁኔታን መፍጠርንና የገቢ ማስገኛ እድሎችን ለማስፋት ያለመ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በፕሮጀክቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በዶሮ እርባታና በምግብ ዘይት ምርት ላይ የተሰማሩ በተለይም ወጣቶች ላይ አተኩሮ አንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

"ፕሮ-አግሮ ኢትዮጵያ" ፕሮጀክት በጀርመን ከሚደገፉ ፕሮግራሞች መካከል መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም