የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶችን ለመሥጠት የጨረታ መወዳደሪያ ሃሳብ መጠየቂያ ሰነድ ተዘጋጀ

125

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለት ብሔራዊ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶቸን ለመሥጠት የጨረታ መወዳደሪያ ሃሳብ መጠየቂያ ሰነድ አወጣ። 

የሃሳብ መጠየቂያ ሠነድ (Request for Proposal) ከፍተኛ ብቃትና ፍላጎት ላላቸው የቴሌኮሙንኬሽን ኩባንያዎች የቀረበ ነው ተብሏል።

በዚህም ኩባንያዎቹ የቴክኒክና የፋይናንስ ብቃታቸውን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን በማቅረብ በጨረታው መሳተፍ እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

በኢትዮ-ቴሌኮም ከተያዘው ፈቃድ በተጨማሪ ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም ሁለት ተጨማሪ ፍቃዶች እንደሚሰጡ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚንስትር ድኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የሃሳብ መጠየቂያ የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ለመክፈት የታቀደው ሥራ አካል ነው ብለዋል።

ይህም ለኢትዮ-ቴሌኮም አጋር ኩባንያ ከመፈለግ ሥራ ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘርፉን ለወድድር ለመክፈት በታቀደው መሠረትም ኩባንያዎች መወዳደር የሚችሉበት የሃሳብ መጠየቂያ ሠነድ ታተሞ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የሃሳብ መጠየቂያ ሰነዱ ለመጪዎቹ ሦስት ወራት ፍላጎት ላላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ክፍት ሆኖ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይደረጋል ነው ያሉት።

በውድድሩም አስፈላጊው የሠነድ ግምገማ በመንግሥት ተካሂዶ አሸናፉ ሁለት ኩባንያዎች እንደሚለዩ ጠቁመዋል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ እንዳሉት ሠነዱን ፍላጎት ያለው ማንኛውም ኩባንያ እስከ ታህሳስ 1ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መግዛት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከታህሳስ 1 እስከ 16 2013 ዓ.ም ደግሞ በጨረታ ሂደቱ ላይ የሚነሱ ጥያዌዎች ባለሥልጣኑ የሚቀበልበት ሲሆን እስከ ጥር 21 በሂደቱ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶ ያልቃል ብለዋል።

የካቲት 26ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 5 ሠዓት ደግሞ ጨረታው ሙሉ በሙሉ ይዘጋል፤ ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም ጨረታውን ያሸነፉ ሁለት ተጨማሪ ኩባንያዎች ፍቃደ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

የሃሳብ መጠየቂያ ሠነድንም ከጥቂት ቀናት በኋላ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የመገናኛ ብዙሃን የማስተዋወቅ ሥራ በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ፍቃዶቹን የመሥጠት ሂደት ከወዲሁ እያከናወነ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በግንቦት 2012 ዓ.ም ባወጣው የፍላጎት መጠያቂያ ከዘጠኝ በላይ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎችና ሁለት የቴሌኮም አገልገሎት ሰጪ ካልሆኑ ኩባንያዎች በድምሩ 11 በጨረታ ላይ ለመሳተፍ የፍላጎት አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም