በአፋር ክልል ቤት ለቤት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት የመስጠት ዘመቻ ተጀመረ

52

ሠመራ፣ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ሶስት ዞኖች ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ (ልጅነት ልምሻ) መከላከያ ክትባት ቤት ለቤት መስጠት መጀመሩን የክልሉ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ለአራት ቀናት በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ከ172ሺ በላይ ህጻናት እንደሚከተቡ ይጠበቃል።

ክትባቱ ዛሬ በሎግያ ጤና ጣቢያ በይፋ በተጀመረበት ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ እንደገለጹት፤ ክትባቱ በክልሉ ገቢ፣ አውሲ እና ሀሪ ዞኖች በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ይሰጣል።

ሶስቱ ዞኖች የተመረጡት በፖሊዮ ቫይረስ የተጠቁ ህጻናት በአጎራባች አካባቢዎች መታየታቸወን ተከትሎ እንደሆነ ገልጸዋል።

ለክትባት ዘመቻው የሚያስፈልጉ ከአንድ ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎች መሰማራታቸውን ያመለከቱት ዶክተር ፈረጅ፤ የግብአትና ሌሎችም ዝግጅቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ልጆቹን በማስከተብ ጤነኛ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንዲወጣ ዶክተር ፈረጅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሠመራ ሎግያ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ማህሙድ ኢብራሂም በከተማ አስተዳደሩ ከ5ሺ በላይ ህጻናት ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ከ100 በላይ የጤና ባለሙያዎች በዘመቻው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም