የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ድጋፍ አደርጋለሁ-ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ

3895

ሶዶ ግንቦት 5/2010 የመንግስትን መረጃ በተደራጀና ጥራት ባለው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት ድጋገፍ እንደሚያደርግ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከወላይታና ዳውሮ ዞኖች ለተወጣጡ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በዘርፉ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና የስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር አለማየሁ አዱኛ በስልጠናው ወቅት እንደተናገሩት የመንግስትን መረጃ በተደራጀ፣ በዘመነና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ለህብረተሰቡ ማድረስ  ተገቢ ነው፡፡

“የማህበረሰቡን የኑሮ ዘይቤ ከስልጣኔ ጋር ለማስተሳሰር የመረጃ ተደራሽነቱ ቀልጣፋ መሆን ይገባዋል” ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሃገሪቱ ባልተለመደ መልኩ የተፈጠሩ ሁከቶች እንዲስፋፉ ያደረገው ወጥነት ያለውና እውነተኛ መረጃ በተገቢው ሰዓት ለተጠቃሚው ባለመድረሱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከፖለቲካ ሽፋን ይልቅ ባለሙያዎች መረጃውን በአግባቡ በመያዝ በህዝብና በመንግስት መካከል የግንኙነት ተግባራቸውን ለመወጣት ኃላፊነት ሊሰማቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉዓለም ዳባ በበኩላቸው በአከባቢው በተመረጡ የመንግስት ተቋማት የመረጃ ፍሰትና የህዝብ ግንኙነትን በተመለከተ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

መረጃን የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብትን ጭምር የሚጋፉ ሂደቶች መኖራቸውን በመገንዘብ   ስልጠና ለመስጠት መነሳሳታቸውን አመልክተዋል፡፡

“የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ለመንግስት ብቻ የሚያደሉ ናቸው” በሚል ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር  መገፋፋትና ልዩነቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩ የተፈጠረው ተደጋግፎ የመሄድ ባህልና አረዳድ ባለማደጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከወላይታ ሶዶ ዞን ዳሞት ፉላሳ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን የመጡት አቶ መሰለ ዶጊሶ ለአካባቢ ገጽታ ግንባታ በሚል ሙያውና ሳይንሱ በማይፈቅደው መልኩ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በዳውሮ ዞን የቶጫ ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ስራ ሂደት አስተባባሪና የስልጠናው ተሳታፊ ወይዘሮ እልፍነሽ ግዛው በበኩላቸው ስልጠናው የነበረባቸውን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት እንዳገዛቸው ገልጸዋል፡፡