በሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያዊያን ለሠራዊቱ ያሳዩት አጋርነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት የጠነከረበት ነው- አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ

62

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2013 (ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሠራዊቱ ያሳዩት አጋርነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት የጠነከረበት መሆኑን ያሳያል ሲሉ በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ ገለጹ።

"የሕወሓት ቡድን" ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በክልሉ የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት እንዳስቆጣቸውና እንዳሳዘናቸው ከዜጎቹ ጋር በነበሩ ውይይቶች መረዳታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃትና ጥቃቱን ተከትሎ እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚረዱና ለሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቁጭትና በተነሳሽነት ለመከላከያ ሰራዊቱ ያሳዩት አጋርነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ይበልጥ መጠንከሩ የታየበት ነው ብለዋል።

ምሁራንን ጨምሮ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለአገሪቱ ባለስልጣናት ገለጻ በማድረግ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲረዱ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ሀብት ማሰባሰብ ስራ መግባታቸውንና  እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ለሳዑዲአረቢያ መንግስትና ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የማስረዳት ስራ መከናወኑን ነው አምባሳደር አብዱልአዚዝ የገለጹት።

በተጨማሪም በሪያድ መቀመጫውን ላደረገው የባህረ ሰላጤ አገራት ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግስትም የሕግ ማስከበር እርምጃው የውስጥ ጉዳይ መሆኑን፤ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለቀጠናው ሰላም ወሳኝ እንደሆነ በመረዳት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልጾልናል ብለዋል።

መንግስት ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑንና ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎችም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ለኢትዮጵያዊያኑ መገለጹን አምባሳደር አብዱልአዚዝ ተናግረዋል።

ኤምባሲው የማህበራዊ ትስስር ገጾች አማራጮችን በመጠቀም በሕግ ማስከበሩ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም