ደቡብ ክልል ከአዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው... ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ

125

ሀዋሳ፤ ህዳር 17/2013( ኢዜአ ) ህገ- ወጡ የህወሃት ጁንታ ያፈናቀላቸው ወገኖችና ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ህወሃት በሀገሪቱ ባለፉት 27 ዓመታት ሲተገብር የቆየውን የሌብነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የዜጎች ሰቆቃ መልሶ ለመድገም በማሰብ በሀይል ወደ ስልጣን ለመምጣት ህገ-ወጥ መንገድ እየተከተለ ይገኛል።

በዚህም ህገ-ወጥ ምርጫ ከማካሄድ ባለፈ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በማድረስ ወንጀል መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ  ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ መንግስት ተደጋጋሚ ሠላማዊ ጥሪ ቢያቀርብለትም ጥሪውን ባለመቀበል ጦርነት አውጆ በሀይል ስልጣን ለመያዝ እየሞከረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህን ተከትሎ መንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻ ውስጥ እንደሚገኝና ክልሉ በጊዜያዊ አስተዳደር  እንዲመራ ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ርስቱ፤ የደቡበ ክልልም በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጁንታው  በክልሉ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን እያወደመ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የጥፋት ቡድኑ ያፈናቀላቸው ወገኖችና ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ  የደቡብ ክልል ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር  አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ሠላምን ከማስከበር አንጻር ጊዜያዊ መንግስት ከመላው የሀገሪቱ ህዝቦችና ክልሎች እንዲሁም ከፌዴራል መንግስቱ ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ነጻ በወጡና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተረከባቸው አካባቢዎች ሠላምን ለማስከበር ከቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ ከህዝብ የተውጣጣ አደረጃጀት በመፍጠር አመራር አዋቅሮ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት ጠቁመው፤  ለዚህም ስልጠና በመስጠትና የአመራር ድጋፍ በማድረግ በኩል ደቡብ ክልል አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በጥፋት ቡድኑ በደል ያልደረሰበት  እንደሌለና በደቡብ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ተላላኪዎቹን  በማሰማራት በርካታ ጥቃቶችን እንዳደረሰ ጠቁመው፤ በዚህ ምክንያትም ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በርካቶች ተፈናቅለዋል ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ባለው ጠንካራ ማህበራዊ እሴትና የለውጡ መንግስት በወሰደው ፈጣን እርምጃ እንደ ብዝሀነቱ  በጥፋት ቡድኑ ልዩነት ለመፍጠር የተደረገው ሙከራ አለማሳካቱን አስታውቀዋል።

ህገ- ወጡ ቡድን በሰራው ጥፋት ለህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ  ሁሉም ክልሎች በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አቶ ርስቱ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም