በኦሮሚያ ክልል የማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፈንድ ሊቋቋም ነው

195

አዳማ ህዳር 16/ 2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል  የማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፈንድ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑን የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲንብሩ እንዳሉት ፈንዱን ለማቋቋም እየሰሩ ያሉት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በጥናትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ የማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋት ነው።

በክልሉ የዜግነት በጎ ፈቃድ አገልግሎትና ሌሎች የማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፕሮግራሞች ተቀርጸው እየተሰሩ ቢሆንም ተቋማዊና በስርዓት የተደገፈ አይደለም ብለዋል።

እየተሰራ ያለውም የጉልበት፣ ቁሳቁስና ገንዘብ ሀብትን በተበታታነ መልኩ ሳይሆን በአንድ ማዕከል ሰብስቦ ህግና ስርዓት ተበጅቶለት ለታለመለት ዓላማ  ማዋል የሚያስችል  ስርዓት የመዘርጋት መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህ ቢሮው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ  ጋር በመተባበር የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከነወነ መሆኑን ጠቅሰው ዕውቀትንና ሳይንሳዊ አሰራርን በተከተለ መልኩ ፈንድን ለማቋቋም ጭምር እንደሆነም አስታውቀዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው የማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፖሊስዎችና ስትራቴጂዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈች የጥናትና ምርምር እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ልማቶች ተጠቃሚ በመሆን ችግሮቻቸውን  ዘላቂነት ለመፍታት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጥናትና ምርምር ውጤት ያስፈልገናል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ከሚያከናውናቸው የምርምር ስራዎች አንዱ ከኦሮሚያ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር የጀመረው የማህበራዊ ደህንነት ፈንድ ማቋቋሚያ ህጎች፣ ስርዓት፣ አሰራርና አደረጃጀት ላይ ጥናትና ምርምር እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም የህግ ማዕቀፎች፣የዘርፉ ፖሊስና ስትራቴጂ ውጤታማነት ላይ  ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማቅረብ የተለያዩ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን መሰረት ያደረገ የምርምር ስራዎች እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፈንድና ስርዓት መዘርጋት ዙሪያ የሚመክር የአንድ ቀን መድረክ በአዳማ ከተማ  ተካሄዷል።

በመድረኩ  በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የጨፌ ኦሮሚያ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ ከሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀትና አካል ጉዳተኞች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።