ጁንታው በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋት ለህዝቡ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው -አቶ ኡሞድ አጁሉ

611

ህዳር 16 /2013 (ኢዜአ) ”ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋት ለህዝብና ሀገር ያለውን ንቀት የሚያሳይ ነው” ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉ አስታወቁ።

የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ለሚያከናውናቸው  ተግባራት እውን መሆን የክልሉ መንግስት  አስፈላጊውን  ድጋፍ  እንደሚደረግም ርዕሰ መስተዳዳሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ ጁንታው ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ሲፈጽመው የቆየው የአፈናና ዘረፋ ተግባር የእራሱን ፍላጎትና ጥቅም ለማሟላት ነበር ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሀገራዊ ለውጥ ጁንታው ቀደም ሲል ሲፈጽማቸው  የነበሩትን   የዘረፋ ፣ጭቆናና  ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች አሁን መድገም ባለመቻሉ  ሀገርን ወደ  ማፍረስ  ዘመቻ ሊገባ መቻሉን ተናግረዋል።

የጥፋት ቡድኑ ወክልሃለው ለሚለው የትግራይ ህዝብ ጭምር የማያስብ ደንታ  ቢስ መሆኑን አፍረሶ የሸሸባቸው ታላላቅ መሰረተ ልማቶች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

የባለፉት ዓመታት በጋምቤላ ክልል ሲፈጽማቸው የነበሩት ዘረፋና የጭቆና ድርጊቶች የጁንታው እንጂ የጭቁኑ የትግራይ ህዝብን የማይወክል መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ከአዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት  ጎን በመሆን ለትግራይ ህዝብ ሠላምና ልማት በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አቶ ኡሞድ  አስታወቀዋል።

የጁንታው አባላትን ለህግ ለማቅረብ እየተከናወነ በሚገኘው  እንቅስቃሴም  የክልሉ  መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን   ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።