በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ የሒሳብ ሥራ ባለሙያዎችን አሰራር ቀልጣፋ የሚያደርግ ስርዓት ተግባራዊ ሆነ

1824

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2010 በግሉ ዘርፍ የሒሳብ ሥራና ተያያዥ ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መጀመሩን የኢትዮጵያ የሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ስርዓቱ የግል ሂሳብ ባለሙያዎች፣  አካውንታንቶች እና ኦዲተሮች ከቦርዱ የሚፈልጉን አገልግሎቶች የጊዜ፣ የወጪ እና የጉልበት ብክነት በመቀነስ ካሉበት ቦታ በቀላል መንገድ ማግኘት የሚያስችላቸው ነው።

በዚህም መሰረት የሒሳብና ኦዲት ፍቃድ፣  የሒሳብና ኦዲት ሰርተፍኬት እድሳት፣ ለአዲስ ሒሳብና ኦዲት የድርጅት ፈቃድ አመልካቾች፣ የሒሳብና ኦዲት የድርጅት ፈቃድ እድሳት ጥያቄዎች እንደዚሁም የሪፖርት አቅራቢ አካላት ምዝገባ አገልግሎቶች የሚሰጡት በኤሌክትሮኒክስ በታገዘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር አዲስ ፍቃድ ለማውጣት፣ ፍቃድ ለማደስ፣ የተፈቀደላቸው የሒሳብ ባለሙያና ኦዲተር ለመሆን ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ግልጋሎቱን ለማግኘት በአካል የመቅረብ ግዴታ ነበረባቸው።

ይህም  የደንበኞችን የጊዜ፣ የገንዘብ እና የጉልበት ብክነት በማስከተል ባለሙያዎች የተለያዩ ቅሬታዎች እንዲያነሱ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አዲሱ የኤሌክትሮኒክስ አሰራር እነዚህን ችግሮች በማስቀረት ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የሚናገሩት።

አሰራሩ በግሉ ዘርፍ ተሰማርተው የኦዲት አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የሒሳብ ሥራ አገልግሎቶችን ለሌሎች አካላት የሚሰጡ ድርጅቶችን አሰራር ወጪና ጊዜን በመቀነሰ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ ነው።

ከዚህም ሌላ አሰራሩ ቦርዱ ባለሙያዎች ስራቸውን በተገቢውና ህጋዊ በሆነ መንገድ እየተወጡ መሆንና አለመሆናቸውን ለመቆጣጠርም ያግዛል ብለዋል።

ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግና አሰራሩን ለማሻሻል ብሎም የባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት በመፈተሽ ቁጥጥር ለማድረግ የሚጫወተው ሚና እንዳለም ጠቁመዋል።

ወደ ፊት ቴክኖሎጂው እያደገ ሲሄድ  ድርጅቶች ሪፖርታቸውን በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚያቀርቡበት አሰራርም ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።