የጀልዱ እና ቶኬ ኩታዬ ወረዳዎች ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ900 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

408

አምቦ  ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን የጀልዱ እና ቶኬ ኩታዬ ወረዳዎች ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ900 ሺህ ብር በላይ በገንዘብና ዓይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡

የጀልዱ ወረዳ ነዋሪዎች በጥሬ ገንዘብ 400ሺህ 200 ብር ለድጋፍ ማሰባሰቡ በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ ማድረጋቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ገቢሳ ገልጸዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ  የወረዳው ህብረተሰብ  ወያኔ ጁንታ  በፈጸመው  የሀገር  ክህደትና ጥቃት በመቆጣት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በገባው መሠረት ለሠራዊቱ  አስተዋጽኦ በማበርከቱ አመስግነዋል።

 ህብረተሰቡ ሠራዊቱ የጀመረውን ህግን የማስከበር ስራ እንዲሳካ  ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የወረዳው ነዋሪ   ወይዘሮ ዲሪቢ ባይሳ  በሰጡት አስተያየት “የአካባቢያችንን ሠላም በመጠበቅና መከላከያ ሠራዊታችንን  ባለን ሁሉ በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንቆማለን” ብለዋል፡፡

ሌላው ነዋሪ አቶ ኪዳኑ ቢሪ በበኩላቸው  “ገንዘብ መስጠት ብቻ ሳይሆን መከላከያ ሠራዊታችንን  አስፈላጊ ከሆነ በአካል ሄደን ድጋፋችንን እናሳያለን” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ  የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪዎች “ድጋፋችን ለመከላከያ ሠራዊታችን ” መሪ ሀሳብ ተነሳስተው  በአስተባባሪዎቻቸው አማካኝነት  17 ሠንጋዎች እና ሰባት   በጎችን  ከግማሽ ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ገዝተው ማበርከታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጉዲሳ ዳንደና ገልጸዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ኃላፊ አቶ አዳሙ ዲንቂሲሳ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየወሰደ ላለው የህግ ማስከበር እርምጃ ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀርበዋል፡፡