በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ ስርአት ለማሻሻል አዲሱ የንግድ ህግ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

221

አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ ስርአት ለማሻሻልና ተወዳዳሪ መለሆን አዲሱ የንግድ ህግ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የተሻሻለውን የንግድ ህግ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተሻሻለውን የንግድ ህግ ረቂቅ አዋጅ ጠቀሜታ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጻ አድርገዋል።

በእዚህም በአገሪቱ ባለፉት 60 ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የንግድ ህግ በተለይ በገበያ መር ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ለትግበራ የማይመች ሆኖ መዝለቁ ተጠቅሷል።

ከዘመኑ ቴክኖሎጂና እድገት ጋር አብሮ ለማራመድ የሚያስችል አቅም የሌለው በመሆኑ ህጉን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑም አብራርተዋል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት አዲስ የወጣው የንግድ ህግ በተለይ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በአሁኑ ወቅት ያለውን የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ የንግድ ስርአት ለመዘርጋትም አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊነት ነባሩ የንግድ ህግ እንዲሻሻል መደረጉም አስፈላጊ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

የተሻሻለው የንግድ ህግ በተለይ የአገሪቱን የንግድ ስርአት ለማዘመን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር አስተዋጽኦው የጎላ ነው።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በርካታ የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶችን እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል።

"በተጨማሪም የንግዱ ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ የንግድ ስርአቱን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል።

በመሆኑም የዓለም አገራትን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ አገራዊ የንግድ ስርአት ህግጋትን ማሻሻል እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ህጉ መሻሻሉ የአገር ውስጥ አቅምን በማጎልበት የንግድ ስርአቱን ቀልጣፋና ዘማናዊ ለማድረግ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

ከተለያዩ አገራት ለኢንቨስትመነት የሚመጡ ባለሀብቶችን ፍላጎትና አሰራር ታሳቢ ለማድረግ እንደሚያግዝም አክለዋል።

ነባሩ የንግድ ህግ ባለፉት 60 ዓመታት ሲሰራበት ቢቆይም ከንግድ ጋር የተያያዙ በርካታ ነገሮች ከመለዋወጣቸው ባለፈ ህጉ ለአፈጻጸም የማይመች ሆኖ መገኘቱም ተገልጿል።

የንግድ ህጉ ተሻሽሎ በአዲስ መተካት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም