ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በራሷ አቅም በህግ መሰረት ትፈታዋለች ... ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

62

አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በራሷ አቅም በህግ መሰረት ትፈታዋለች” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፤ ኢትዮጵያ በሉዓላዊ አገር ላይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ እንዲከበር አጥብቃ ትሻለች።

ኢትዮጵያ ረጅምና አኩሪ ታሪክ እንዳላት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሲመሰረት መስራች አባል እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ሲመረት የላቀ ሚና የተጫወተች አገር መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የባለብዙ ዘርፍ ትብብርና የዓለም ስርዓት በመርህና በህግ መሰረት እንዲፈጸም ጽኑና የማይናወጥ አቋም እንዳላት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ምንጊዜም በህግ ላይ ለተመሰረተ የዓለም ዓቀፍ ስርዓት ድጋፏን በተግባር እየገለጸች እንደምትገኝ አስታውሰዋል።

ለአብነትም በተመድና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በተለያየ የዓለም ክፍል ተሳትፎ ማድረጓን አንስተዋል።

በተመድ ቻርተር አርቲክል 2(7) እንደተቀመጠው የዓለም ዓቀፍ የህግ ስርዓት መሰረታዊ መርህ በሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን እንደሚደነግግ አስታውሰዋል።

የዓለም አቀፍ ፍርድ ሸንጎም በተደጋጋሚ ይህንን በማረጋገጥ “ጣልቃ ያለመግባት መርህ አንድ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳዩን ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት መፍታት አንዱና ወሳኙ እንደሆነ ያትታል … የዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ትብብርም ይህንን መሰረታዊ መርህ በማክበር የሚከናወን ነው” ይላል ሲሉ አመልክተዋል።

ይህ መሰረታዊ መርህ በአፍሪካ ህብረት የህግ ስርዓት ውስጥ መካከቱን ገልጸዋል።

የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ አሳስቧቸው ላሳዩት ፍላጎት መንግስት እንደሚያደንቀውና እንደሚረዳው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ዘመቻውን የውስጥ ጉዳይዋ በመሆኑ በራሷ እንደምትፈታው አመልክተዋል።

የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈልግ ከሆነም መንግስት ጥያቄ ሲያቀርብ ብቻ የሚፈጸም እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

በአትዮጵያ የመጣው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህወሃት ጁንታ ከዚህ በተቃራኒ ሲጓዝ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የህወሃት ጁንታ ለውጡን በመቀልበስ በሃይል ወደስልጣን ለመምጣት ፍላጎት እንዳለውም አመልክተው፤ ላለፉት ሶስት አመታት ያህል የቡድኑ አመራሮች በአገሪቱ ሁከት እንዲፈጠር ሰዎችን ሲያሰለጥኑ፣ ሲያሰማሩ፣ ሲያስታጥቁና በገንዘብ ሲደግፉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይህ ቡድን በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።

“ይህ ደግሞ የአገሪቱን ህግ የመጣስ ወንጀል ነው” ብለዋል።

በዚህ ያላበቃው ቡድኑ በማይካድራ 600 ያህል ንጹሃንን ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አምነስቲ አነርናሽናልና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የአገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅና ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ዘመቻ መሆኑን አመልክተዋል።

ሉዓላዊ የሆነችው ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ህግ የማስከበር ስራዋን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንደምታከናውን አረጋግጠዋል።

ዘመቻውም በአፍሪካ ከህገመንግስታዊ መንገድ ውጭ ወደስልጣን መምጣትን በሚከለክለው የዴሞክራሲ፣ የምርጫና የአስተዳደር ቻርተር መንፈስና ዓላማ መሰረት የሚከወን መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት በዘመቻው ንጹሃን እንዳይጎዱ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ ስለመሆኑም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም