የትግራይ ክልል ሴቶች የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ኮንፈረንስ ተጀመረ

99
አክሱም ግንቦት 5/2010 ክልል አቀፍ የሴቶች የሰላም፣የልማትና የዴሞክራሲ ኮንፈረንስ ዛሬ በአክሱም ከተማ ተጀምሯል። በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ  የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር እንደገለጹት የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠልና ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሴቶች የጀመሩትን ሁለንተናዊ ትግል አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ በተለይ አደረጃጀታቸውንና የልማት ቡድናቸውን በማጠናከር ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን የበለጠ ማጠናከር  እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ ''ሴቶች ለሰላምና ዴሞክራሲ በታገሉት ልክ  ተሳታፊ እና ተጠቃሚ አልሆኑም'' ያሉት ወይዘሮ ፈትለወርቅ በዚህ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በኮንፈረንሱም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮችንና ሊስተካከሉ የሚገባቸው አሰራሮችን በመፈተሽ የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ''የኮንፈረንሱ አላማ በክልሉ ሴቶች ጉዳይ ያልተሻገርናቸውን ችግሮች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥና  የሴቶችን  ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የበለጠ ማሳደግ ነው'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ደክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል ናቸው፡፡ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ  ከሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች የተውጣጡ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም