የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በስልጣን መጋራትና በአስተዳደራዊ መዋቅር ጉዳዮች ላይ ቅድመ ስምምነት አደረጉ

72
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2010 የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በስልጣን መጋራትና የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር ጉዳዮች ላይ ቅድመ ስምምነት ማድረጋቸው ተገለጸ። የሱዳን መንግስት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በተሰጠው ውክልና መሰረት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንትን ሳልቫኪርን እና የቀድሞ ምክትላቸው ሬክ ማቻርን በካርቱም በማደራደር ላይ ይገኛል። የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በአገሪቱ የሽግግር አስተዳደር ወቅት ሊኖር በሚገባው መንግስታዊ የአስተዳደር መዋቅር እና በስልጣን መጋራት ጉዳዮች ላይ ድርድር በማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። መንግስታዊ የአስተዳደር መዋቅሩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እና የህግ አውጪው ምክር ቤት አባላት ቁጥር መወሰንን ጨምሮ የተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው ተብሏል። በነዚህ ጉዳይ ላይ የተደረሰው ስምምነት ነገ ይፈረማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የመጨረሻውና የተሟላው ስምምነት ደግሞ በመጪው ሳምንት የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በሚገኙበት ስነ-ስርዓት እንደሚፈረም የቻይና ዜና አውታር ዥንዋ ዘግቧል። ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን ከአራት ዓመት በላይ የቆየውን ግጭት በማስቆም በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ያመጣል የሚል ተስፋ የተጣለበት መሆኑን የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ገልጿል። ቀደም ሲል በተካሄዱት የሰላም ድርድሮች ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ ለማቆምና የጦር ኃይሎቻቸውን ከከተሞች አካባቢዎች ለማራቅ ተስማምተዋል። እንዲያም ሆኖ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ባለፈው ሳምንት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ጥሏል። በአሜሪካ መንግስት አነሳሽነት የቀረበው የማዕቀብ ውሳኔ ሀሳብ 15 አባላት ካሉት የፀጥታው ምክር ቤት መካከል ድጋፍ የተቸረው በዘጠኙ ሲሆን ኢትዮጵያን፣ ሩሲያንና ቻይናን ጨምሮ ስድስት አገራት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እንደገለፁት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለማድረግ የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፍ “በሰላም ጥረቱ መጓተት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሰላቸቱን” የሚጠቁም መልእክት ለደቡብ ሱዳን ተፋላሚ አካላት መሪዎች ያስተላልፋል በማለት ገልፀዋል። በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአምባሳደሯ በኩል ማዕቀቡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሰላም ለማምጣት የተጀመረውን ጥረት አደጋ ላይ ይጥለዋል በሚል የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በመቃወም ተከራክራለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም