ለውጡን ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን እንቃወማለን ... የእስልምና ሐይማኖት አባቶች

61

መቱ፤ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ የሚደረግ ጥረት እንደሚቃወሙ በኢሉ አባቦራ ዞን የእስልምና ሐይማኖት አባቶች ገለፁ። 

የዞኑ እስልምና ምክር ቤት ጉባኤ በመቱ ከተማ ተካሄዷል።

የሐይማኖት አባቶቹ  በወቅቱ እንደገለጹት  ሀገራዊ ለውጡን ተከተሎ ካለፉት ሁለት  ዓመት ወዲህ የሙሰሊሙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

የኢሉ አባቦር ዞን ኡላማዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ አብደላ ጀማል ለኢዜአ  እንደገለጹት  ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግስት የሙስሊሞችን ጥያቄ በመቀበል መፍትሄ እንዲያገኙ  በትኩረት እየሰራ ነው:።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ወኪሉን በነፃነት አንዲመርጥና ፍላጎቱን መሰረት ያደረገ የባንክ  አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"ሀገራዊ ለውጡን ለመቀልበስና ወደ ኋላ ለመመለስ  የሚደረግ ጥረት መብቶቻችንን የሚጻረር በመሆኑ እንቃወማለን" ብለዋል ።

የኦሮሚያ ክልል ኡለማዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሐጂ ሻፊ አህመድ በበኩላቸው ሀገራዊ  ለውጡን ተከትሎ ሙስሊሙ ማህበረሰብ  የታፈነው መብቱ በመረጋገጡ  እምነቱን  በነፃነት  እያራመደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለያዩ አካባቢዎች ለውጡን ለመቀልበስና ሰላም ለማደፍረስ በሚጥሩ አካላት ላይ  መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚደግፉም  አስታውቀዋል።

በጉባኤው ላይ በእንግድነት የተገኙት የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ  ጀምበሬ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሀገሪቱ የልማትና ዕድገት ጉዞ ላይ እያሳየ ያለውን  ተሳታፊነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በሐይማኖት ስም ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩ አካላትን  ነቅቶ  በመጠበቅ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅዎ እንዲያጠናክር ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም