በአማራ ክልል የከተማ መሬት አስተዳደርና አመራርን ለማዘመን እየተሰራ ነው

93

ደብረብርሀን ህዳር 14ቀን 2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል የከተማ መሬት አስተዳደርን፣ አሰራርንና አመራርን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የከተማ መሬት ይዞታና ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ገለጹ።

ኤጀንሲው  በደብረ ብርሃን ከተማ 50 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ ያስገነባው  ባለ አራት ፎቅ ህንጻ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት  የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽቤ ክንዴ እንዳሉት  መንግስት የከተማ መሬት አስተዳደርን፣ አሰራርንና አመራርን  ለማዘመን እየሰራ ካለው ውስጥ በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባው ህንጻ  ተጠቃሽ ነው።

ይህም  የመሬት  ይዞታ መረጃዎችን ለማዘመን፣ የመሬት ሀብት ብክነትን ለመቀነስና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እንደሚያመች ተናግረዋል።

የመሬት አና መሬት ነክ መረጃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጅ በመጠቀም በአንድ ቋት በማደራጀት በዘርፉ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ጭምር እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

በምረቃው ሥነ -ሥርዓት በክብር እንግድነት  የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት የህንጻው መገንባት ፈጣን እድገት ለማስመዝገብና የተገልጋዮችን እርካታ ለመፍጠር የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።

የከተማ እድገት ሊለካ የሚችለው ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት ያለውን የመሬት ሀብት ቆጥሮ በመያዝ በግልጽ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ በበኩላቸው  ከተማዋን ለኢቨስትመንትና ኑሮ ምቹ በማድረግ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን  ለመሳብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም እያደገ የመጣውን የኢቨስትመነት ፍሰትና የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ለመመለስ የመሬት ይዞታ አያያዝን ማዘመን ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው ያስገነባው ህንጻም ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም