የመጠጥ ውሃ ችግራቸው በመፈታቱ መደሰታቸውን የሊበን ጃዊ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ

100
አምቦ ሀምሌ 11/2010 ቀደም ሲል የነበረባቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በመፈታቱ መደሰታቸውን በምዕራብ ሸዋ ዞን የሊበን ጃዊ ወረዳ  ነዋሪዎች ገለፁ። የወረዳው ውሃና ኢነርጅ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በባቢች ከተማ የተገነባው የውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ በሊበን ጃዊ ወረዳ የባቢች ከተማ ነዋሪ አቶ ሙርቲ ነገዎ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ውሃ ባለመኖሩ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በቀን እስከ ሁለት ሰዓት ይጓዙ ነበር፡፡ አሁን ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ኘሮጀክት በቤታቸው የውሃ መስመር አስገብተው ተጠቃሚ በመሆናቸው ለዓመታት የነበረባቸውን ችግር እንደተፈታላቸው ገልፀዋል፡፡ በዚሁ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ደሚቱ ገመቹ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የነበረው የውሃ ችግር እንደእሳቸው ላለ አቅመ ደካማ ሰዎች ይበልጥ አስቸጋሪ እንደነበር   አስታውሰዋል፡፡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘትም ረጅም ሰዓት በእግር ለመሄድ አቅማቸው ስለማይፈቅድላቸው የመጠጥ ውሃ ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት ጎሮቤቶቻቸውን ሲያሥቸግሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በቤታቸው የቧንቧ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው ከዚህ ቀደም የነበረባቸው ችግር እንደተፈታላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ " ከዚህ ቀደም የመጠጥ ውሃ ዕጥረት ያለብን በመሆኑ ረጅም ርቀት በመሄድ ንፅህናው ያልተጠበቀ የምንጭ ውሃ  ስንጠቀም ለተለያየ የውሃ ወለድ በሽታ ስንጋለጥ ቆይተናል "  ያሉት ደግሞ የሊበን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀቤሣ ሚልኬሣ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዲስ በተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው ከተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታ ስጋት ነጻ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡ የሊበን ጃዊ ወረዳ ውሃና ኢነርጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ጫንዶ በበኩላቸው በአካባቢው የነበረው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ለረጅም ጊዜ መቆየቱን ተናግረዋል። የህበረተሰቡን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ በ42 ሚሊዮን ብር ስራው የተጀመረው የውሃ ፕሮጀክቶች በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስረድተዋል። አገልግሎት መስጠት የጀመረው የውሃ ኘሮጀክት በአምስት ቀበሌዎች የሚገኙ ከ31 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎችን ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት አስተማማኝ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የወረዳው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንም ቀደም ሲል ከነበረበት 52 በመቶ ወደ 66 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም