ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ረጲ የሀይል ማመንጫን ጎበኙ

79

አዲስ አበባ፤ ህዳር 14/2013(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከኢትዮጵያ መብራት ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ እና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫን ጎበኙ።

የሀይል ማመንጫው አልፎ አልፎ የሚያጋጥመውን የግብዓት አቅርቦት እና የበጀት ችግር መቅረፍ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ከስራ ኃላፊዎቹ ጋር ተወያይተዋል።

ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሀይል ማመንጫ በ32 ሄክታር መሬት ላይ በአመት 185 ጊጋ ዋት ሀወር የኤሌትሪክ ሀይል የሚያመነጭ ሲሆን፤ አሁን ላይ የገቢ አቅሙ ገና በመሆኑ የግብዓትና የበጀት ችግር እንደገጠመው የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ብሩክ ኤባ ገልፀዋል።

ምክትል ከንቲባዋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታን የጎበኙ ሲሆን በውስጡ ያሉ ሰራተኞችን በገጠማቸው ችግሮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል።

በዚህም መሟላት የሚገባቸውን የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፤ ቦታው ከመጥበቡ የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እየፈጠረ ስላለው ጫና የከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ለማ አብራርተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በተቋሙና አካባቢው ላይ ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ አካላት ያላቸውን ክብር እና ምስጋና በመግለጽ ፤ አስተዳደሩ ለተነሱ ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት አብሯቸው እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም