ለመከላከያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ጥሪ - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ጥሪ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2013(ኢዜአ) ለአገሩ ዘብ የቆመውን የመከላከያ ሠራዊት በክህደት ከጀርባው የወጋው የጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የሚመራው ቀድሞ የሠራዊቱ ባልደረባ በነበሩ ከሃዲ የጦር መኮንኖች መሆናቸውን እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ተናግረዋል።
ይህንንም እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ለውጊያ ያሰለፋቸውና አቅጣጫ ሲሰጣቸው የነበረው ብርጋዴር ጄኔራል አብርሃ ተስፋዬ (ድንኩል) እንደሆነ ይናገራሉ።
እጃቸውን ለመከላከያ ከሰጡ የልዩ ሃይል አባላት መካከል ጸጋዬ ዮሃንስ በመጀመሪያ በፖሊስ አባልነት ቢገባም ሳይፈልግ ‘መሬትህን እንወስድብሃለን' በማለት በግዴታ ወደ ልዩ ሃይል እንዳዛወሩት ይገልጻል።
ነጋሲ ገብረኪዳንና በሪሁ አብራሃለይ ከግል ስራቸው ወደ ልዩ ሃይል እንዲገቡ ተደርገው ከ3 እስከ 6 ወራት ስልጠና እንደተሰጣችው ይገልጻሉ።
ወደ ውጊያ የተሰለፉትም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ሳይሆን ሌላ ጠላት መጥቷል፣ ክልላችን ተወሯል በሚል በፅንፈኛው ቡድን ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን ይናገራሉ።
እጃቸውን ያልሰጡ የልዩ ሃይል አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት እጃቸውን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
በሠራዊቱ ወስጥ የ10 አለቃ ማዕረግ እንደነበረው የሚናገረው ገብረኪሮስ ገብረሃና በ13ኛ ክፍለ ጦር አባልነት ቆይቶ ከሠራዊቱ ኮብልሎ ወደግል ስራ ተሰማርቶ መቆየቱን ይገልጻል።
በክልሉ ልዩ ሀይል እንዲገባ ተጠይቆ ፈቃደኛ ባይሆንም በግዴታ "ይሙት ይዳን ከማላውቀው ወንድሜ ጋር ወደልዩ ሃይል እንድንገባ ተደርገናል" በማለት ወደ ግንባር መምጣቱን ይገልጻል።
በህወሓት አመራሮች በኩል የሚሰጠውና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ እንደሆነ በመግለጽ፤ 'የብልጽግና ጦር ሊወርህ ነው፣ መደምሰስ ነው' በሚል ወደውጊያ እንደተሰማሩ ገልጿል።
በተመሳሳይ አስማረ አብርሃ ከ2002 እስከ 2008 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ቆይቶ በመጨረሻም ኮብልሎ በትውልድ ቦታው በግል ስራ መቆየቱን፤ በቅርቡም በአካባቢው ሚሊሻ በአጋዥነት እንደተመለመለ ይገልፃል።
ታጣቂዎቹ ሕዝቡ ጦርነት እንደማይፈልግ፤ ነገር ግን የቀበሌ አገልግሎት ለማግኘት እንኳን ሳይወድ በግድ መጠቀሚያ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
ልዩ ሃይሉም በሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን በግዴታ ወደጦር ግንባር መዝመቱን ገልጸው፤ “ያለ ዕድሜያቸው በጫካ በከንቱ መቅረት የለባቸውም” ብለዋል።
የጽንፈኛው ህወሓት አባላት እጃቸውን ሰጥተው ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር በሠላም መኖር እንደሚገባ ገልጸዋል።
19319310 Comments27 SharesLikeCommentShare