ደኢህዴን ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄን ለማፋጠን የድርሻውን ይወጣል

76
ሀዋሳ ሀምሌ 11/2010 የህዝቦችን ሰላምና አንድነት በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄ ለማፋጠን የድርሻውን እንደሚወጣ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን/ አስታወቁ፡፡ የየአካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ የተገመገመበትና ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የደኢህዴን አመራሮች የተሳተፉበት  መድረክ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመድረኩ በተለይ በክልሉ በተወሰኑ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ  አለመረጋጋቶችና ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተመልክቷል፡፡ አለመረጋጋትና ግጭቱ የዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመስራት መብትን የገደበና እርስ በእርስ መጠራጠርን እያሰፋ ያለው ከስተት ለመቀልበስ በጋራ መረባረብ የአመራርነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እንደዜጋም ግዴታ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገር ደረጃ ከተጀመረው  የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ የማይሄድና በህዝቦች የዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ የአመራሩንም አቅም በተለያየ መልኩ ያመከነ በመሆኑ ሁኔታውን ቆም ብሎ መፈተሽ አመራሩና አባሉ የተጣለበትን አደራ በራስ መተማመን መንፈስ ተንቀሳቅሶ መወጣት ይኖርበታል ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው፡፡ ሀገራዊ የለውጥ ንቅናቄውን በመጋራት ሂደት የህዝቦች ጥቅሞች የሚያረጋግጡ አመራጮችን ማስፋትና ዲሞክራሲውን ማጠናከር ይገባል፡፡ ለዚህም  አመራሩና አባሉ  እያጋጠሙ ያሉ ብዥታዎችና ክስተቶችንም ከስር ከስር መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ ደኢህዴን ላለፉት ዓመታት የክልሉን ህዝቦች በማታገል አሁን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ የተሻገረው ችግሮችን የመፍታት ብቃት ስላለውና  ያጋጠሙትን ቀውሶች መቀልበስ በመቻሉ መሆኑን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ ድርጅቱ እዚህ የደረሰው በርካታ እልህ አስጨራሽ ፈተናዎችን በማለፍ ነው፤ አሁን ያጋጠመውን ፈተና መቀልበስና ወደ መልካም እድል የመቀየር ጉዳይ የአመራሩ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ደኢህዴን ያጋጠሙት ችግሮች መሰረታዊ መነሻቸው ውስጣዊ ድክመቶች መሆናቸውን በመድረኩ የጋራ አቋም መያዙን መግለጫው ጠቅሶ ይህንን ለማስተካከል በየደረጃው የሚገኘው አመራር ከተዛቡ አዝማሚያዎች ፈጥኖ በመውጣት የየአካባቢውን ጉድለቶች ፈጥኖ ማረም የሚያስችል ጠንካራ እንቅስቃሴ ማደረግ ሲችል ነው ብሏል፡፡ የህግ የበላይነትንና ተጠያቂነትን የማረጋገጡ ተግባር በሁሉም ደረጃዎች እንዲጠናከር አቅጣጫ መቀመጡን ያመለከተው መግለጫው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን የህገወጥነት አዝማሚያ ከወዲሁ ካልተቀጨ የከፋ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል መገምገሙን ገልጿል፡፡ በዚህም ረገድ ድርጅቱ የህዝቡን ጸጥታና ደህንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጧል፡፡ አለመረጋጋትና የጸጥታ ስጋት ሰፋ ባሉ የክልሉ አካባቢዎች እየተስተዋለ መሆኑን የጠቀሰው የድርጅቱ መግለጫ ይህም በህዝቡ የተለመደ የአብሮነት የትብብርና የመፈቃቀር ስነልቡና ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ይህን ሁኔታ ለመቀየር ህብረተሰቡን የማወያየትና የመንግስት መዋቅሩን ተልዕኮውን እንዲወጣ የማድረግ ስራ በስፋት እንደሚከናወን አስታውቋል፡፡ በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ እንዲሁም አማሮ ወረዳ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ለተፈናቀሉ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ  ከማጠናከርና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ከመፍጠር አኳያ የተጀመረው  እንቅስቃሴ መቀጠል አለበት ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው፡፡ በተመሳሳይ ችግር በሀዋሳና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት የመመለሱ ተግባር በአፋጣኝ እንዲከናወን ድርጅቱ ወስኗል፡፡ በክልሉ የህዝቦችን ሰላምና አንድነት በማጠናከር በሀገር ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲፋጠን ደኢህዴን የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአመራሩ መድረክ  ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ማምሻውን መጠናቀቁን የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡          

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም