በሠራዊቱ ላይ ጥቃትና ዘረፋ ከመፈፀማቸው በፊት ከህወሓት ሰዎች ጋር ሲዶልቱ የነበሩ የጦር መኮንኖች ነበሩ -- ከጥቃቱ የተረፉ የጦር መኮንን

74

ህዳር 12/2013 (ኢዜአ) በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃትና ዘረፋ ከመፈፀሙ በፊት በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ሆነው ከህወሓት ሰዎች ጋር ሲዶልቱና ሠራዊቱ ትጥቅ እንዳያሟላ ሲያደርጉ የነበሩ የጦር መኮንኖች ነበሩ - ከጥቃቱ ያመለጡት ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ። 

በአገር ጉዳይ አንዳች ልዩነት የማይንፀባረቅበትን ሠራዊት የፖለቲካ መጠቃሚያ ሲያደርግ የቆየው የህወሓት ቡድን አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተደረገው ወታደራዊ ሪፎርም ተከፍቷል።

የሠራዊቱ አዲስ አደረጃጀት ከአንድ ብሔር ተላቆ ሁሉን አሳታፊ በሆነ አግባብ መሆኑ ለሠራዊቱ ቢመችም ሠራዊቱ ውስጥ ሆነው ለህወሃት ለሚሰሩ ጥቂት መኮንኖች ግን ምቾት አልሰጣቸውም።

ከጥቅምት 24ቱ የከሃዲዎች ጥቃት ለምስክርነት የተረፉት የ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ወታደራዊ አመራር ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ ከጥቃቱ በፊት በክልሉ ስለተስተዋሉ ድርጊቶችና መረጃዎች ይገልጻሉ።

በወታደራዊ ሪፎርሙ ያልተደሰቱ የሠራዊቱ አመራሮች ብሔር ተኮር ዝንባሌ በማንገብ፤ የመንግስትን አቅጣጫ በመጣስ ጥቅማቸው ተነክቶባቸው መቀሌ የመሸጉ የህወሓት ዘራፊ ቡድንን አመለካከት መያዛቸውን ይናገራሉ።

ህወሓት በጡረታ የተገለሉ የጦር መኮንኖችን በክተት አዋጅ በመጥራት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለክልሉ ልዩ ሃይል የመድፍ፣ የታንክ፣ የአየር መቃወሚያና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር ነው የሚገልጹት።

በሠራዊቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም እንደሆነ በመጠርጠር ለክፍለ ጦር አዛዡ ብናመለክትም አቅም ካላቸው 'ከዚህም በላይ የፈለጋቸውን ቢያሰለጥኑ ምን አገባን' በሚል የሠራዊቱን ጥርጣሬ አለመቀበላቸውን ገልጸዋል። 

አመራሮቹ ቀን ቀን ከሠራዊቱ ጋር ከአንገት በላይ ሲያወሩ፤ ማታ ማታ ግን መቀሌ ከመሸጉት የህወሓት ሰዎች ጋር ልብ ለልብ ሲመሳጠሩና ሲያሴሩ ነበር ይላሉ ሻለቃ አምሳሉ።

ይህንን ደግሞ በሠራዊቱ ላይ በክህደት በተፈጸመው ጥቃት አረጋግጠናል ነው ያሉት።

የሜካናይዝዱን አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴን ጨምሮ በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ አመራሮች ወታደራዊ የሪፎርም ስራውን ሲያስተጓጉሉ እንደነበረም ገልፀዋል።

ለአብነትም ሠራዊቱ ወታደራዊ ትጥቅ እንዳያሟላና ግዳጁን እንዳይወጣ ከአዲስ አበባ አስከ መቀሌ በየቦታው ባለው መዋቅራቸው በመጠቀም የከባድ መሳሪያ መለዋወጫ ከወትሮው በተለየ እንዲዘገይ ሲያደርጉ እንደነበር ያነሳሉ። 

ሠራዊቱን በብሔር በማቧደን ለማወክና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ ሠራዊቱን የማፍረስ ሴራ ሲያሴሩ እንደቆዩም ያነሳሉ።

ለዚህም በሠራዊቱ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነት የሚሰሩ የራሳቸውን ሰዎች በማዋቀር በጥቃቱ ወቅት ዓላማቸውን ለማሳካት እንደተጠቀሙባቸው ገልጸዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ከሠራዊቱ ጋር ለዓመታት የኖሩ የራሳቸውን ሰዎች በማደራጀት፣ የትና በማን እጅ መሳሪያ እንዳለ የሚጠቁሙ የውስጥ አባላትን በሙሉ ወደራሳቸው ወገን በማድረግ ነው።

የጦር መሳሪያ መጋዘኑን ቆልፈው ወታደሩ መሳሪያ እንዳያወጣ በማድረግ በልዩ ሃይል እንዲከበብ ያደረጉትም ቀድሞ ሲያሴሩ የነበሩ ከአዛዥ ጀምሮ በካምፑ ውስጥ ነዋሪዎች እንደነበርም ተናግረዋል።

ከክፍለ ጦር እስከ ብርጌድ አመራር ያሉ ከሃዲያን አመራሮች በአንደበታቸው ከሠራዊቱ፣ በልባቸው ግን በብሔርተኝነት ተዘፍቀው ወደ አንጃው ቡድን በመግባት ሲዶልቱ፣ በሁለት ቢላ ሲበሉ እንደነበር ገልፀዋል።

ጡረታ የወጡ የቀድሞ አመራሮቹም ወደ ወታደራዊ ካምፕ እየመጡ በዝግ ሲወያዩ ይስተዋል እንደነበር አስታውሰዋል።

ሠራዊቱ በስፍራው በቆየባቸው ዓመታት ከትግራይ ሕዝብ ጋር በፍቅር መኖሩን፣ ሕዝቡም ከጠላት ከሚጠብቀው ሠራዊት፣ ከደሞዙ ቀንሶ ከሚያግዘው፣ አንበጣ ከሚከላከልለት ሠራዊት ጎን እንደሆነ ገልጸዋል።

ድርጊቱን የፈጸሙት በአንድ ሠራዊት ውስጥ ሆነው በብሔር አመለካከት የተዘፈቁ መኮንኖች ጥቅማቸው ከተነካባቸው የህወሓት ሰዎች ጋር በመመሳጠር መሆኑንም ተናግረዋል።

የህወሓት ሰዎች ሲቪሎችን በመላክ በከተማ የሚንቀሳቀሱ የሠራዊቱን አባላት ማንነት ተኮር ስድብ በማሰደብ፣ አንዳንዴም ድብደባ እንዲፈፀምባቸው በማድረግ ሠራዊቱን በመተንኮስ ወደ ሌላ ነገር እንዲገባ ቢጥሩም ሠራዊቱ ግን ሁሉንም በትዕግስት ማክሸፉን ገልጸዋል።

ይህ ሕዝብና ሠራዊቱን የማጋጨት ሴራቸው አልሳካ ሲል በመጨረሻ ራሳቸው በመግባት ጦር ሠራዊቱን በክህደት ጥቃት እንደፈጸሙበት ሻለቃ አምሳሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም