በሀዋሳ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና ሠንጋዎች ተበረከተ

58

ሀዋሳ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) ህግ ለማስከበር ግዳጅ ላይ ለተሠማራው ለጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊት በሀዋሳ ከተማ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና 41 ሠንጋዎች ድጋፍ ተደረገ። 

ድጋፉ የተገኘው  ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎችና የተለያዩ ድርጅቶች ነው፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ካንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ድጋፉ በተደረገበት ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዳሉት የህወሃት ጁንታ  በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላየ የፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ ይቅር የማይለው ነው።

ቡድኑ በስልጣን ቆይታው ለሀገር ክብር ቦታ እንዳልነበረው ጠቁመው ሀገራዊ ለውጡን ባለመቀበል የፈጠረውን ችግር ለማስወገድ ወደ ህግ ማስከበር  መገባቱን ተናግረዋል።

ከነዋሪዎችና  ድርጅቶች የተደረገው ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩ ባደረገው የአንድ ቀን ንቅናቄ የተሰበሰበ መሆኑንና ህዝቡ ለሃገር መከላከያ ያለውን አክብሮትና ፍቅር ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡

ግዳጁን በአጠረ ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ መደበኛ የልማት ተግባር ለመመለስ እየታገለ ያለው የመከላከያ ሠራዊት ተገቢ ክብርና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አራት ሠንጋዎችን ያበረከቱት አቶ ያንጣራ ሚና በሰጡት አሰተያየት ከጥፋት ቡድኑ  ጋር እየተፋለመ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ባደረጉት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንና እገዛቸውንም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የሰገነት የሴቶች ቁጠባ ማህበር ተወካይ ወይዘሮ አበበች ቢወጣው በበኩላቸው ማህበሩ  የ10 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ወገኔ ነው ብሎ ባላሰበበትና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ በህወሀት ጁንታ የደረሰበት ጥቃት የቡድኑን ክፉ ባህሪና ጭካኔ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ቡድኑን ሥርዓት ለማሲያዝ የተጀመረው ህግ የማስከበር ተግባር ጊዜው እንዲያጥር ወገን የሆነው የትግራይ ህዝብ መተባበር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

ለሠራዊት የ50 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረጉት የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ጀማል አደም በበኩላቸው የህወሀት ጁንታ ቡድን ከዚህ በፊት ህዝቡን በተለያየ መልኩ በመከፋፈልና ሠላም እንዳይኖር በማድረግ ልማታችንን ሲያጓትት የቆየ ነው ብለዋል።

አሁን ካደረጉት በላይ ለመደገፍ  ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ህግን ለማስከበር በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመለክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም