ማህበሩ 1 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ

42

ድሬዳዋ ህዳር 10/13(ኢዜአ) የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች አለም አቀፍ ማህበር 1 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያ ለድሬዳዋ ጤና ቢሮ በድጋፍ አበረከተ። 

 የማህበሩ ተወካይ ሞዴሊስት ፈቲሃ መሐመድ መመርመሪያ መሳሪያውን ትላንት ለአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስረክበዋል።

ተወካይዋ በወቅቱ እንደገለፁት በአስተዳደሩ እየተካሄደ ያለውን የኮሮና መከላከልና መቆጣጠር ስራ ለማገዝ ድጋፉ ተደርጓል።

ማህበሩ ከአንድ ወር በፊት ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጭ የተገዙ ምግቦችን  ለህጻናትና ለአረጋዊያን ማህበራት መለገሱን በማስታወስ ወደፊት መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክታለች ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው አስተዳደሩ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በትውስት ባገኘው መሳሪያ ምርመራውን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

ከማህበሩ በድጋፍ የተገኘው መሳሪያ የምርመራውን  አቅም በእጥፍ እንደሚያሳድገው አመላክተዋል።

"በመደጋገፍና በመተባበር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማሳካት ይገባል" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ።

የድሬዳዋ ጤና ቢሮ የድንገተኛ አደጋዎች ላብራቶሪ ጥናትና ምርመራ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ኢብራሂም አብዱልሃሚድ "በድጋፉ የተገኘው የመመርመሪያ መሳሪያ  ለድሬዳዋና ለአካባቢው የተሟላ ምርመራ ለመስጠት ያግዛል" ብለዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ መሳሪያው አሁን ያለውን በቀን 250 ናሙና የመመርመር አቅም  በእጥፍ ያሳድገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም