የፓርኮችን ደህንነት ለማስጠበቅ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል ተባለ

111

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/2013 (ኢዜአ) ብሔራዊ የዱር እንስሳት ፓርኮችን ሁሉን አቀፍ ሥነ-ምህዳራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣንን የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አፈፃፀምን ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ ገምግሟል።

የዱር እንስሳት የሚኖሩባቸው ብሔራዊ ፖርኮች ሥነ-ምህዳራቸው ተጠብቆ ደህንነት እንዲሰማቸው ለማድረግ በየደረጃው ካሉ አደረጃጀቶች ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ ገልጸዋል።

“በፓርኮቹ አካባቢ የሚኖረውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የባለቤትነት መንፈስ መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ባለሥልጣኑ በፓርኮቹ አካባቢ የሚስተዋሉትን ሕገ-ወጥ ተግባራት ለመከላከል ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ካሉ መዋቅሮች ጋር በቅንጅት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

በዱር እንስሳት መኖሪያዎች አካባቢ መጤ አረምን ማጽዳትና የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን በመጠበቅ ለእንስሳቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ባቀረቡት ሪፖርት የ10 ዓመት መሪና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዶች ተዘጋጅቶ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ላይ መስራት ለፈለጉ 50 ግለሰቦች ፈቃድ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል።

በቀይ ቀበሮ ጥናትና ክትትል፣ በሥነ-ምህዳራዊ ልማትና ጥበቃ፣ በደን አስተዳደር፣ በፓርኮች ጽዳትና ጥበቃ መስኮች ለ396 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።

በፓርኮች ከ68 ሄክታር መሬት በላይ ችግኞችን በመትከል የክትትልና እንክብካቤ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በዱር እንስሳትና በፓርኮች አያያዝ ዙሪያ ጥናቶችን ለመስራት የተጀመሩ ስራዎች ስለመኖራቸውም ገልጸዋል።

60603 SharesLikeCommentShare

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም