በጭቆና ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ህዝብ ነፃ የሚወጣበት ቀን ሩቅ አይደለም - አቶ ርስቱ ይርዳው

63

ሀዋሳ ህዳር 08/2013 (ኢዜአ) ህግን ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ በጭቆና ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ህዝብ ነፃ የሚወጣበት ቀን ሩቅ አይደለም ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ። 

አቶ ርስቱ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ስግብግቡ የህወሓት ቡድን የሀገር ህልውና የሆነውን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ባልጠበቀው መንገድ በማጥቃት የህዝቡን ክብር የሚነካ ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ፈፅሟል።

በተለይ የሰሜን ዕዝ ከ20 ዓመት በላይ በትግራይ ክልል በቆየባቸው ጊዜያት የሀገርን ድንበር ከመጠመቅ ባለፈ የትግራይን ህዘብ በልማትና ማህበራዊ ጉዳዮች  ሲያግዝ የኖረ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ምንም እንኳን የጥፋት ኃይል በሆነው ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ጥቃት ቢፈፀምበትም የሚቃጣበትን ማንኛውንም ትንኮሳ የመመከት ፅናት ያለው የማይበገር የህዝብ ልጅ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት  የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት በጥፋት ቡድኑ ላይ እርምጃ እየወሰደ ህግ የማስከበር ስራውን  በጀግንነት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አቶ ርስቱ ሠራዊቱ እያደረገ ያለው የሀገርን ህልውና የማስጠበቅና ህግን ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ  አስረድተዋል።

በዚህም በፅንፈኛው ህወሓት በጭቆና ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ህዝብ ነፃ የሚወጣበትና ዳግም የኢትዮጵዊያን ወንድማማችነት የሚጠናከርበት ቀን ሩቅ አይደለም ብለዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ከታደሙት መካከል ወይዘሮ ፋናዬ ሙሉነህ በሰጡት አስተያየት የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈፀመው ጥቃት በእጅጉ አሳምሞናል ብለዋል።

ለመከላከያ ሠራዎታችን ድጋፋችንን በአደባባይ ከመግለፅ ባለፈ በገንዘብም ሆነ በሚጠበቅብን ማንኛውም ኃላፊነት ለመወጣት ከጎኑ እንቆማለን ብለዋል።

ሌላው ታዳሚ በደቡብ ክልል ልዩ ኃይል የአድማ ብተና አንደኛ ሻለቃ ሶስተኛ ሻምበል አዛዥ ዋና ሳጅን አርባ ጮሎ በበኩላቸው የህወሓት የጥፋት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ከሀዲ ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ  የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በማንኛውም ጊዜ ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ   ጎን በመቆም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር በተዘጋጀው ሥነ- ሥርዓት  የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ ሌሎች አመራሮች፣  ፖሊስ፣ ልዩ ሃይልና የመንግስት ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

 ለሀገር ሉዓላዊነትና የህግ የበላይነት እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብርን የሚንጸባረቅ  ዜማና  ትርኢት በክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም