ቱርክ ኢትዮጵያ የምታካሂደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በአግባቡ ትረዳለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ

1213

አዲስ አበባ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) የቱርክ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሚያካሂደውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በአግባቡ እንደሚረዳ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ጋር መንግስት እያካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዙሪያ በስልክ ተወያይተዋል።

እየተካሄደ ስላለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓላማ ምንነት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ለቱርኩ አቻቸው በዝርዝር አብራርተዋል።

በማብራሪያቸውም የህወሃት ጁንታ በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ አሳፋሪ ጥቃት መፈጸሙንና እዙ የታጠቀውን መሳሪያ ለመዝረፍ መሞከሩን ተናግረዋል።

የጁንታው ድርጊት የወንጀል ብቻ ሳይሆን የአገር ሉዓላዊነትን የመዳፈርና የክህደት ድርጊት መሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት ይህንን ወንጀለኛ ጁንታ ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝና በክልሉ የህግ የበላይነትን እንደሚያረጋግጥ ጠቅሰዋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ በበኩላቸው “የቱርክ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ እያካሄደ የሚገኘውን የህግ ማስከበር ዘመቻ በአግባቡ ይረዳል” ብለዋል።

ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።