መንግስት ህግና ስርዓት ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን-- በኬንያ እና ማላዊ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን

50

አዲስ አበባ ህዳር 06/2013 (ኢዜአ) መንግስት ህግና ስርአት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ በኬንያ እና ማላዊ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ። 

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኬንያ እና በማላዊ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ በበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም በእዚህ ወቅት እንዳሉት ስግብግቡ የህወሓት ጁንታ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ዘግናኝና አሳዛኝ ጥቃት በመፈጸም ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለአገር ደንታ ቢስ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

የእዚህን የጥፋት ቡድን እንቅስቃሴ የተረዱት በኬንያ እና በማላዊ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከመንግስትና ከህዝብ ጎን እንደሚቆሙ በውይይቱ ወቅት ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ህግና ስርዓት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ መስማማታቸውንም ተናግረዋል።  

ኢትዮጵያዊያኑ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመደገፍ የጀመሩትን የቦንድ ግዢ ለመቀጠል ቃል መግባታቸውንም ነው አምባሳደር መለስ የገለጹት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፅዮን ተክሉ በበኩላቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ቡድን ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ለውጦችን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

አገራዊ ለውጡ ያልተዋጠላቸው የጥፋት ኃይሎችም ለውጡን ለማስቆም በተቃራኒው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል የሚፈልገው የህወሓት ጁንታ አገርን ለማተራመስ የሚያደርገውን እኩይ እንቅስቃሴ መንግስት የማስቆም ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተጨማሪም የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን የማረጋገጥና የንፁሀን ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን መንግስት እንደሚወጣም ነው ያስረዱት።

በአግር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዜጎች የመንግስትን ህግ የማስከበር ጥረት በመገንዘብና በልማት ሥራዎች በመሳተፍ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ግስጋሴ እንዲያግዙ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም